የኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሥራ እድል ለመፍጠር ይዞት የነበረው እቅድ አፈፃፀም እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ተገለፀ

64
አዲስ አበባ ህዳር 24/2011 የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የዜጎችን የሥራ እድል ለማስፋት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ። በምክር ቤቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኮሚሽኑን የ2011 የመጀመሪያ ሶስት ወራት የሥራ ክንውንና የ100 ቀን እቅድን ገምግሟል። ኮሚሽኑ በተጠቀሰው ጊዜ የሥራ እድል ለመፍጠር ይዞት የነበረው እቅድ አፈፃፀም እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ለቋሚ ኮሚቴው በቀረበው ሪፖርት ላይ ተመልክቷል። የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት ከ41 ሺህ በላይ ዜጎችን የቋሚ ሥራ ባለቤት ለማድረግ ታስቦ ነበር፤ ሆኖም የተፈጠረው ሥራ ከ5 ሺህ ብዙም ያልዘለለ ነው። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው መለስ እንዳሉት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ፣ ቴክኖሎጂና እውቀት ምንጭ ከመሆን ባሻገር ለዜጎች ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል በመሆኑ ትልቅ ትኩረትን ይሻል። "ስለኢንቨስትመንት ሲወራ የስራእድል ፈጠራ የማይታለፍ ጉዳይ ነው" ያሉት ሰብሳቢው ሆኖም ኮሚሽኑ በሩብ አመቱ የፈፀመው ካቀደው አንፃር ዝቅተኛ ነው ብለዋል። በመሆኑም ኮሚሽኑ ለስራ እድል ፈጠራ ትኩረት በመስጠት የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ እንዳለበትም ነው ቋሚ ኮሚቴው ያሳሰበው። መንገድ፣ ውሃና ኤሌክትሪክን ጨምሮ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ የሚስተዋሉ የመሰረተልማት ችግሮችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባም ኮሚቴው አስገንዝቧል። እንዲያም ሆኖ ኮሚሽኑ በሩብ ዓመቱ ያከናወናቸውን የተሻሉ አፈፃፀሞች አድንቋል። በተለይም 54 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ወደሥራ ለማስገባት አቅዶ 42ቱ ማሳካት መቻሉን፤ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር በተያያዘ ያሉ አገልግሎቶችን በመመዝገብ ረገድ ያከናወናቸው ተግባራት በጥንካሬ ተገምግመዋል። መረጃዎችን ተንትኖ ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች ተደራሽ በማድረግ የተከናወነው ሥራንም ምክርቤቱ አድንቋል። የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ፍፁም አረጋ በሰጡት ማብራሪያ በሥራ እድል ፈጠራ ላይ የታየው ዝቅተኛ አፈፃፀም በአገሪቱ ተከስቶ ከነበረው አለመረጋጋት ጋር የተያያዘ የተፈጠረ ነው ብለዋል። ከዚሁ ጋርም ኮሚሽኑ አዳዲስ ኢንቨስትመንት ከመሳብ ይልቅ የነበሩትን ማቆየት በሚቻልበት ስልት ላይ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱም ሌላው ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል። በተለይ በኤሌክትሪክ ኃይልና ጉምሩክ ላይ የሚስተዋለውን የቅንጅታዊ አሰራር ችግር ለመፍታት በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል። ቋሚ ኮሚቴው ከሩብ አፈፃፀም በተጨማሪ የኮሚሽኑን የ100ቀናት እቅድ ገምግሟል፤ በቀጣይ የሚኖሩትን የግምገማ መመዘኛ ነጥብና የክትትልና ቁጥጥር መርሃግብርን በተመለከተም ለኮሚሽኑ ማብራሪያ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም