የመዲናዋ ተግባራትን ለማወቅና ምርምር ለማድረግ የሚያግዝ የመረጃ ቋት ተዘጋጀ

76
አዲስ አበባ ህዳር 24/2011 በአዲስ አበባ የሚከናወኑ ተግባራትን ለማወቅና ተጨማሪ ምርምር ለማድረግ የሚያግዝ የመረጃ ቋት ማዘጋጀቱን የከተማዋ ሬዚላንስ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ገለጸ። ከሶስት አህጉራት የተውጣጡ ስምንት ችግሮችን የመቋቋም ችሎታ ያላቸው (ሬዚላንስ) ከተሞች የትስስር አባል አገራት የተሞክሮ ልውውጥ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። የአዲስ አበባ የሬዚላንስ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ፍፁም-ብርሃን ፀጋዬ በዚህ ወቅት እንዳሉት ባለፈው ዓመት ወደ ስራ የገባው ፅህፈት ቤቱ የከተማዋን ችግሮች የመቋቋም ችሎታ ለማሳካት የሚያስችል ፍኖተ-ካርታ አዘጋጅቷል። በዚህም በዘርፉ የወጡ ፖሊሲዎችን፣ የተከናወኑ እና የሚከናወኑ ተግባራትን የሚያሳይ የመረጃ ቋትን ማደራጀቱን ተናግረዋል። ከአንድ ወር በኋላ ይፋ የሚደረገው የመረጃ ቋት ለሁሉም አካላት መረጃ በመስጠትና ድግግሞሽን በማስቀረት ሃብትን ከብክነት ይታደጋል ብለዋል። የመረጃ ቋቱ መዘጋጀት በቀጣይ በአዲስ አበባ የተሰሩና ያልተሰሩትን ተግባራት ለማወቅና ተጨማሪ ምርምር ለማድረግ ያግዛል ነው ያሉት። አዲስ አበባ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካላዊ ጫናዎችን ለመቋቋም ፈቃደኛ በመሆን በዓለም ካሉ 100 ሪዚላንት አገራት አንዷ ሆናለች። የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ እንዳሉት አዲስ አበባ በልምድ ልውውጡ ተሳታፊ ከሆኑት ከአፍሪካ፣ ደቡብ አሜሪካና ከእስያ አገራት ከተሞች የተሻለ ልምድ ታገኛለች። ከከተማ እድገት ጋር ተያይዞ መደበኛ ያልሆነው የአኗኗር ዘይቤ ማደግ ድንገተኛና ቋሚ ችግሮችን የሚፈጥር በመሆኑ አዲስ አበባን ብቻ ማሳደግ ወይም ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት መስራት ብቻውን ውጤት አያመጣም ብለዋል። በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በከተማዋ ዙሪያ ያሉ አካባቢዎች ክፍተቶችን ጎን ለጎን መፍታት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት ችግሮችን ተቋቁሞ ተስማሚ ከተማን ለመፍጠር እንዲቻል ፍልሰትና የቤት ልማት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል። የአፍሪካ ሬዚላንስ ፕሮግራም ዳይሬክተር ካሮሊና ራየስ በበኩላቸው በአዲስ አበባ ከተማ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ከማሳተፍ አንፃር ክፍተት ይታያል። ኢኮኖሚው ላይ ካለው ስራ አጥነት አንፃርም መደበኛ የሆነውን የከተማዋን እንቅስቃሴ ባልጎዳ መልኩ በመስራት መደበኛ ያልሆነውን ዘርፍ ለማሳደግ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አስታውቀዋል። የአዲስ አበባ ከተማም ከመኖሪያ ቤት ልማትና ከጎርፍ አወጋገድ ጋር ተያይዞ የሌሎችን ከተሞች ልምድ መውሰድ እንዳለበትም ጠቅሰዋል። የደቡብ አፍሪካዋ ኬፕታውን ከተማ ኢ-መደበኛ በሆነው ዘርፍ አቅዶ ከመስራት አኳያ በርካታ ልምድ እንዳላት አመልክተዋል። በአዲስ አበባ ጫናዎች ተብለው የተለዩት ዋና ዋናዎቹ ስራ አጥነት፣ የቤት ችግር፣ ድህነትና ሙስና ሲሆኑ ከከተማዋ እድገት ጋር ተያይዞ እየተባባሱ መጥተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም