ኢትዮጵያ የአየር ብክለትን መለካት የሚያስችል በቂ የብክለት መቆጣጠሪያ ጣቢያ ሊኖራት ይገባል – በተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ፕሮግራም

948

አዲስ አበባ ህዳር 24/2011 ኢትዮጵያ የአየር ብክለትን መለካት የሚያስችል በቂ የብክለት መቆጣጠሪያ ጣቢያ ሊኖራት እንደሚገባ የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ፕሮግራም ገለጸ።

የአየር ብክለት በዓለም ላይ ለሰው ልጆች ሞት መንስኤ ከሆኑ አስር ምክንያቶች አንዱ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ያሳያል።

ከኢንዱስትሪዎች፣ ተሽከርካሪዊችና ሌሎች ከባቢ አየር በካይ ጉዳዮች ምክንያት በዓለም ላይ በየዓመቱ ከሶስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለህልፈት ይዳረጋሉ።

በኢትዮጵያም ጉዳዩ ከሌሎች የዓለም አገሮች አንጻር ሲታይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ ባይሆንም በቦትስዋና፣ ቤኒንና ኢትዮጵያ በየዓመቱ እስከ 94 ሺህ ዜጎች በዚሁ ሳቢያ ህይወታቸውን ያጣሉ።

በተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ፕሮግራም አማካሪ አደሪያና ምባንዲ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የአካባቢ አየር ብክለት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ መለየት የሚያስችል በቂ የመቆጣጠሪያ ጣቢያ የላትም።

ኢትዮጵያ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ቢኖሯትም የአካባቢ አየር ብክለት መቆጣጠሪያ ጣቢዎች በሶስት ከተሞች አዲስ አበባ፣ ሀዋሳና አዳማ ብቻ የተወሰኑ ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም የአካባቢ አየር ብክለት ምን ደረጃ ላይ እንዳለና የጉዳት መጠኑን ለመለየት ተጨማሪ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች እንደሚያስፈልጓት ጠቁመዋል።

ኢንዱስትሪዎች በብዛት ያልተስፋፉና ያሉትም ከብክለት ነጻ ቢሆኑም እንኳ ትራንስፖርት፣ ኃይል ማመንጫዎች፣ ግንባታዎች አማካኝት የካባቢ አየር እንደሚበከል ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የብክለት መጠኑን በየጊዜው መቆጣጠር እንደሚገባ አሳስበዋል።

በአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ከፍተኛ የአየር ብክለትና ቁጥጥር ባለሙያ አቶ መሰረት አብዲሳ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ያለው የአካባቢ አየር ብክለት መጠን ለክፉ የሚሰጥ አይደለም ብለዋል።

ይሁን እንጂ አሁን የሚስተዋለው ጅምር የብክለት ደረጃ በዚህ ከቀጠለ አደጋው የከፋ ሊሆን ስለሚችል ለጉዳዩ ከዚህ በላይ ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ከአገሪቷ የህዝብ ቁጥርና የቆዳ ስፋት አንጻር አሁን ያሉት የብክለት መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች በቂ ባለመሆናቸው ችግሩን ለመከላከል ተንቀሳቃሽ መሳሪያዎችን እየተጠቀሙ መሆኑንም ተናግረዋል።

የብክለት መጠኑ ከቦታ ቦታ የተለያየ መሆኑን የገለጹት ባለሙያው፤ ከውጭ የሚገቡ አሮጌ መኪናዎች ግንባር ቀደም የአከባቢ አየር በካይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አዳዲስ መኪናዎች ሲገቡ የሚከፈለው ቀረጥ ከአሮጌዎቹ በእጥፍ ስለሚበልጥ አስመጭዎች ለአሮጌዎች ቅድሚያ እንዲሰጡ አድርጓቸዋልም ብለዋል።

በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ከብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲና ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር ውይይት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።