አክሱም ህዳር ጽዮን

1793

ደሳለው ጥላሁን-ኢዜአ-የታሪክ ድርሳናት እንደሚያትቱት  “አክሱም” የሚለው ቃል “አኩ” በአገውኛ ቋንቋ ውኃ ማለት ነው፡፡ “ሱም” ደግም የሴም ቋንቋ ሲሆን ትርጉሙም “ሹም” እንደ ማለት ነው፡፡  በአክሱም ሰሜናዊ ክፍል አንድ የውኃ ጉድጓድ አለ፡፡ እሱም “ማይሹም” ይባላል፡፡ የከተማዋ መጠሪያም ከዚህ የውሃ ጉድጓድ የተወሰደ እንደሆነ ብዙዎቹ ይስማማሉ።

መንግሥትና ጥንታዊ መዲና  የነበረችው አክሱም የተለያዩ የዘርፉ ምሁራን እንደሚያትቱት የሃይማኖት ማዕከል፣የጥንት ሃይማኖታዊ መንግሥትን በአፍሪካ ውስጥ የመሰረተች፣የኃያላን መንግሥትና በአሁኑ ሰዓትም ቢሆን ወደ ስፍራው የሚያቀኑ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ አገር እንግዶችን የምታስተናግድ  ከተማ ነች፡፡

የታሪክ ተመራማሪው ፍራንሲስ አንፍሬ እንደሚገልፁት የአክሱም መንግስትና ከተማ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዓለም ከሚገኙት አራት መንግስታት ከሮም፣ከፋርስና ከቻይና ቀጥሎ አራተኛ ኃያል መንግስት ነበረች፡፡

በአሁኑ ሰዓት በአክሱም የሚገኙት የጥበበኞች እጅ ያረፈባቸው ግዙፍ ሐውልቶች፣የነገስታት መቃብሮች እንዲሁም የማይዳሰሱ ቅርሶች  የንግሥተ ሳባ አፈ ታሪክ፣ ቀዳማዊ ምኒልክ ከእስራኤል ያመጣው ጽላትና የቅዱስ ያሬድ ዜማ የአክሱም ጥንታዊ ታሪክ ምን ያህል ሃያል እንደነበረ ማሳያዎች ናቸው፡፡

አክሱም ጽዮን(ርዕሰ አድባራት ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ጽዮን) በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ትገኛለች፡፡ በመጀመሪያ የክርስትና ሃይማኖትን ወደ ኢትዮጵያ ይዞ በገባው አቡነ ሰላማ ዘመን እንደተገነባች የሚነገርላት የአክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን በዮዲት ጉዲት በመፍረሷ አሁን የተገነባው የአክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ በአጼ ኃይለ ስላሴ ዘመን እንደተሰራ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡

የንግስተ ሳባ አፈታሪክ እንደሚያትተው ንግስተ ሳባ ጥበብን ፍለጋ የተለያዩ ስጦታዎችን በመያዝ ወደ ኢየሩሳሌም ታሪካዊ ጉዞ አድርጋለች፡፡

ከስያሜዋም ጋር ተያይዞ በአዲስ ኪዳን ንግስተ አዜብ(የደቡቧ ንግስት) ስትባል በኦሪት ንግስተ ሳባ በመባል ትጠራለች፡፡ ሮማኖች ኒኮል፣የመኖች በልክስ እንዲሁም ኢትዮጵያዊያን ማክዳ በማለት ይጠሯት ነበር፡፡

በኢየሩሳሌም ጉዞዋ ምክንያት የተወለደው ቀዳማዊ ምኒልክ ከአደገ በኋላ በ12 ዓመቱ ከእናቱ የተሰጠውን ለታቦተ ጽዮንና ለንጉሥ ሰሎሞን እጅ መንሻ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘ፡፡ ንግሥት ሳባም ለንጉሥ ሰሎሞን “ንጉሥ ሆይ ልጄን ሙሴ የጻፋቸውን ሕግጋት ሥርዓተ ክህነት አስተምረህ ላክልኝ፡፡” የሚል መልእክት ልካ ነበር፡፡ ቀዳማዊ ምኒልክ በኢየሩሳሌም ከአባቱ ዘንድ ለሦስት ዓመት ያህል ቆይቷል፡፡ አባቱን ከኢየሩሳሌም ጎብኝቶ ሲመለስ የአክሱም ጽዮን ጽላትን በመያዝ ህዳር 21 ቀን አክሱም እንደገባ ይነገራል።

ይህች ታቦት ለ3000 ዓመታት ያህል እስከዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ በአክሱም ትገኛለች፡፡ ንግሥት ሳባም ታቦተ ጽዮን መምጣቷን ስትሰማ ለእግዚአብሔር መስዋዕት አቀረበች፡፡ ሰዎችን መርጣ ታቦተ ጽዮንን እንዲጠብቁ አድርጋለች፡፡ የመንግሥቱን ሥልጣን በሙሉ ለቀዳማዊ ምኒልክ አስረክባ ከዚህ ዓለም በሞተ በተለየች ጊዜ በዚያው በአክሱም ተቀብራለች፡፡ ቦታውም እስከ አሁን ድረስ የንግሥት ሳባ መቃብር እየተባለ ይጠራል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምሮ የሙሴ ጽላት “ታቦተ ጽዮን” የሚለውንም ስያሜ ያገኘችው ጽዮን ተብላ በምትጠራው የእስራኤል ከተማ ስም ነው፡፡ ጽዮን ማለት ተፀወነ፣ ተጠጋ፣ ተማጠነ ማለት ነው፡፡ ጽዮን የተባለችው የታላቁ የዳዊት ከተማ የተገፉና የተበደሉ ሕዝቦች ሁሉ እውነተኛ ፍርድ ለማግኘት፣ ተሰብስበው የሚሰነብቱባት ከተማ ነበረች፡፡ ጽላተ ሙሴም በዚያ ስለነበረች በርሷ ተማጽነውም ችግራቸው ሰለሚቃለል ታቦቷ “ታቦተ ጽዮን” መባሏ ይተረካል።

እጅግ የከበረና መለኮታዊ ትእዛዛት የሰፈሩበት ጽላትና ማደሪያው የሆነው ታቦቱን በተመለከተ ቢያንስ ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት የት እንደተሰወረና በማን እጅ እንዳለ እንኳን እስራኤላውያንን ጨምሮ መላው አለም ከአንዳንድ መላ ምቶች በስተቀር ተጨባጭ የሆነ መረጃም ሆነ ማስረጃ የለውም።

ነገር ግን አገራችን ኢትዮጵያ መላው ዓለም እንቆቅልሽ የሆነበትን እጅግ የከበረ፣ ታላቅና መንፈሳዊ ቅርስ ባለቤት፣ ጠባቂና ባለ አደራ ሆና እየጠበቀች እንዳለ በጉዳዩ ላይ የተጻፉ መጽሐፍትና የዘርፉ ምሁራን ዋቢ ምስክር ናቸው፡፡

እንደ ግራሃም ሃንኮክና እንደ ጀምስ ብሩስ የመሳሰሉት የውጭ አገር ጸሐፍት የሙሴ ጽላትን ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸውም በላይ የጠፋውን ጽላት ለማግኘት ያደረጉትን ጥረት በመጻሕፍት መልክ ማቅረባቸው ጽላተ ሙሴ በታሪካዊቷ ከተማ አክሱም ሰለመገኘቷ ሌላው ማሳያ ነው፡፡

በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው የታሪክ ጸሐፊው አቡሳላህ “አቢሲኒያውያን በእግዚአብሔር ጣቶች አሥርቱ ቃለት የተጻፈባት፣ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ያሉባት የቃል ኪዳኑ ታቦት አለቻቸው፡፡” በማለት ጽፎ ነበር፡፡

የሙሴ ጽላት ወደ ኢትዮጵያ (አክሱም) መምጣት በተለያዩ ታሪካዊ መረጃዎች እንደተጠቀሰው የውጭና የሃገር ውስጥ ጥናቶችም እንደሚያረጋግጡት  ከኢትዮጵያ በቀር “እስካሁን እኛ ጋር ነው ያለው” የሚል ሌላ ሃገር ፈጽሞ አለመኖሩ  በእርግጥም የሙሴ ጽላት አክሱም ስለመኖሩ አመላካች ነው፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አስተምሮ ህዳር 21 ቀን ታቦተ ጽዮን ዳጎንን ገልብጣ በመጣል ኃይሏን የገለጠችበት ዕለት ነው፡፡ በፍልስጥኤማውያን ተማርካ ቤተ ጣዖት ወስደው ከጣዖታቸው ከዳጎን በታች አስቀምጠዋት ነበር፡፡ ታቦተ ጽዮን ግን በላይዋ ያለውን ዳጎንን ገልብጣ ጥላ እርሷ ከላይ ተቀምጣለች፡፡

ምንም እንኳን የዓለም ማህበረሰብ የሙሴ ጽላትን የጠፋው ጽላት በማለት ስለ መጥፋቱ አያሌ መላምቶችን ቢያስቀምጥም ኢትዮጵያውያን ግን በየአመቱ ህዳር 21 ቀን በአክሱም በመሰባሰብ በዓሉን ያከብራሉ፡፡

ክብረ በዓሉም በኢትዮጵያ በአደባባይ ደምቀው ከሚከበሩ ባህላዊና ሃይማኖተዊ በዓላት መካከል አንዱና ዋነኛው መሆኑ ይነገራል።

ይህ ታሪካዊ ቀንም ከሀገር ውስጥና ከውጭ በተሰበሰቡ የበዓሉ ታዳሚዎች በየአመቱ ይከበራል፡፡

በኢትዮጵያ በአደባባይ ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት አንዱ የሆነው የአክሱም ህዳር ጽዮን በዓል ዘንድሮም ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር በተሰባሰቡ የእምነቱ ተከታዮች፣ ቱሪስቶች፣ የሃይማኖት አባቶች የትግራይ ክልልና የፌዴራል መንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፡፡

የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት መረጃ እንደሚያስረዳው በዘንድሮ የህዳር ጽዮን ክብረ በዓል ወደ አንድ ሚሊዬን የሚጠጉ የበዓሉ ታዳሚዎች ተገኝተዋል፡፡ በክብረ በዓሉም ከአለፉት ሁለት አስርት አመታት በላይ ከኢትዮጵያዊያን ወንድም እና እህቶቻቸው ጋር ተለያይተው የነበሩ ኤርትራውያን በአክሱም በመገኘት በዓሉን አክብረዋል፡፡

በክብረ በዓሉ ላይ የቃለ ቡራኬ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያሪክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ለአመታት ተለያይተው የቆዩት ሁለቱ ሲኖዶሶች አንድ በመሆን ከኤርትራዊያን ወገኖች ጋር ማክበር መቻላቸው የዘንድሮው የህዳር ጽዮን በዓልን ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡

“ለሰላም የሚመጥን ዋጋ የለውም” ያሉት ፓትሪያርኩ ሰላም ትልቅ ሃብትና ጸጋ መሆኑን በመገንዘብ ህዝቡ ጸንቶ መጠበቅ እንዳለበት አባታዊ ምክራቸውን ለበዓሉ ተሳታፊዎች አስተላልፈዋል፡፡

አማኞች ህዳር ጽዮንን በአክሱም፣ ልደትን በላሊበላ፣ ጥምቀትን በጎንደር እና ሌሎችንም በዓላት ከወገኖቻቸው ጋር በድምቀት ሲያከብሩ ቢኖሩም አሁን ላይ በሀገሪቱ እየተስተዋለ ያለው የዜጎች የመንቀሳቀስ ህገ-መንግስታዊ መብት ስጋት እንደገጠመው በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ተናግረዋል፡፡

ታዲያ ለዚህ በአገር ላይ ለተደቀነ ስጋት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ በመቆም ሊታገል እንደሚገባም በዚህ አጋጣሚ ምክትል-ርዕሰ መስተዳደሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከኤርትራ ለመጡ አንግዶች የአንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የሁለቱን ሃገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ እየተደረገ ያለው ጥረት እንዲጠናከር ኢትዮጵያዊያን ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።በዓሉ የጋራ አብሮነት፣መተሳሰብና መጠያየቅን የሚያበረታታ እንደመሆኑ የሁለቱ ህዝቦች ወንድማማችነት ወደፊትም በማይነጣጠል መልኩ እንደሚቀጥል በዕለቱ ቃል ገብተዋል።

ኢትዮጵያ ከማይዳሰሱ ቅርሶቿ አንዱ የሆነውን የገዳ ሥርዓት በ2009 ዓ.ም ኅዳር 21 ቀን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት/ዩኔስኮ/ በቅርስነት ስታስመዘግብ በዚሁ ቀን የጥንቷ መዲና አክሱም የኅዳር ጽዮን በዓልን በአደባባይ እያከበረች ነበር፡፡

የዘንድሮው የአክሱም ህዳር ጽዮን ክብረ በዓል አካል የሆነውና ከበዓሉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የተካሄደው የፓናል ውይይት የአክሱም ህዳር ጽዮን ሃይማኖታዊ የአደባባይ ክብረ በዓልን በዩኔስኮ በማይዳሰሱ ቅርሶች ማስመዝገብ ላይ ትኩረት አድርጎ መካሄዱ ለሃይማኖታዊ ክብረ በዓሉ ትኩረት ስለመሰጠቱ ማሳያ ነው፡፡

በዓሉን በቅርስነት ለማስመዝገብ በተጀመረው ጥረት ግብዓት ለማሰባሰብ ታሳቢ ተደርጎ በተዘጋጀው በዚህ የፓናል የውይይት መድረክ  የቤተክርስትያን ሊቃውንት፣ ታዋቂ ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ነበሩ፡፡

በመድረኩ ላይ “የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች እና ያላቸው ጠቀሜታ″ በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አማካሪ ዶክተር ህያብ ገብረጻዲቅ  ኢትዮጵያ ያሏትን የማይዳሰሱ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶችን ለዓለም ማህበረሰብ በማስተዋወቅ  ተጠቃሚ መሆን እንዳለባት ጠቁመዋል፡፡

‘‘አንድን ቅርስ በአለም ቅርስነት ለማስመዝገብ መሟላት ያለባቸው መስፈርቶች አሉ‘‘ያሉት ጥናት አቅራቢው የአክሱም ህዳር ጽዮን ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ለአለም ማህበረሰብ ካለው አስተዋጽኦ፣ ለአካባቢው ህብረተሰብና ለሀገር ከሚኖረው ጠቀሜታ አንጻር የሚጠየቀውን መስፈርት ስለሚያሟላ  መመዝገብ እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡

በፓናል ውይይቱ የማይዳሰሱ ቅርሶች ትውፊታቸውን ይዘው እንዲዘልቁና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩ የሚያስችል የሃሳብ ግብአቶች መገኘታቸውን የተናገሩት የአክሱም ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመድህን ፍጹምብርሃን ናቸው፡፡

በዓሉን በአለም የቅርስ መዝገብ ለማሰመዝገብ  የበዓሉን ሃይማኖታዊና ታሪካዊ አመጣጥ፣ የበዓሉ ተሳታፊዎች አለባበስ፣ የበዓሉ የአከባበር ሥነ ሥርዓት፣ በበዓሉ ላይ የሚቀርቡ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ዝማሪዎችና ጨዋታዎች፣ በየአመቱ በዓሉን ለማክበር ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር በሚመጡ እንግዶች እና መሰል ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሰነድ የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ ነው፡፡

በፓናል ውይይቱ ላይ የተገኙት የርዕሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ካህናት አባ ተክለሃይማኖት አሳየኸኝ በዓሉ በአለም ቅርስነት እንዲመዘገብ  ቤተ ክርስትያኗዋ ዘወትር  ስትጠይቅ መቆየቷን አስታውሰዋል፡፡

”የህዳር ጽዮን ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል  የሀገር ሀብትና  ቅርስ እንደመሆኑ መጠን ሀገር አቀፍ በዓል መሆን አለበት” ያሉት አባ ተክለሃይማኖት ክብረ በዓሉ በቅርስነት እንዲመዘገብ በሚደረገው ጥረት  ህዝብና መንግስት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ታዲያ ለዚህ ታሪካዊና ታላቅ ሃይማኖታዊ የአደባባይ ክብረ በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት/ዩኔስኮ/ በማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ እንዲመዘገብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ርብርብ ማድረግ አይገባም ትላላችሁ፡፡ ሰላም፡፡