የእንስሳት ክትባት በአቅራቢያችን ማግኘታችን የእንስሶቻችንን ጤና ለመጠበቅ አስችሎናል.. አርሶ አደሮች

155
ደብረብርሀን ህዳር 24/2011 የእንስሳት ክትባት በአቅራቢያቸው ማግኘታቸው የእንስሶቻቸውን ጤና በዘመናዊ መንገድ ለመጠበቅ እንዳስቻላቸው በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ። አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል በደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪ አርሶ አደር በየነ ኃይሉ እንዳሉት ቀደም ሲል በአካባቢያቸው በእንስሳት ጤና አጠባበቅ ላይ የህብረተሰቡ ግንዛቤ አናስተኛ ነበር። በተጨማሪም በአካባቢያቸው የእንስሳት ጤና ኬላ ባለመኖሩ እንስሳት ሲታመሙ ለማሳከምና ለማስከተብ 5 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመንዳት ይገደዱ እንደነበር አስታውሰዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእንስሳት ጤና አጠባበቅ ላይ የህብረተሰቡ ግንዛቤ እያደገ በመምጣቱ አንድ ጤና ኬላ በህዝብ ተሳትፎ በአካባቢያቸው በመገንባቱና የጤና ባለሙያ በመመደቡ ዘመናዊ ሕክምናና ክትባት በቅርበት ለማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል። "በቀጣይም የተደራጁ ወጣቶች የእንስሳት መድኃኒት እንዲያቀርቡ ለማድረግ በገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበራት በኩል ዝግጅት እየተደረገ ነው" ብለዋል። በመንዝ ማማ ምድር ወረዳ የቀበሌ 02 ነዋሪ አርሶ አደር ግዛው አለሙ በበኩላቸው ቀደም ሲል እንስሳትን በልማዳዊ መንገድ ከማከምና መድኃኒት ከመስጠት ውጭ ክትባት እንደማያውቁ ተናግረዋል። በእዚህም በርካታ እንስሳት እንደሞቱባቸው የገለጹት አርሶ አደሩ "በአሁኑ ወቅት ግንዛቤያችን እያደገ በመምጣቱ እንስሶቻችንን በማስከተብ ጤናቸው ማስጠበቅ ችለናል" ብለዋል። በተያዘው ዓመት ብቻ 27 የሚደርሱ በግ፣ የዳልጋና የጋማ ከብቶችን በበሽታ ከመያዛቸው በፊት በማስከተብ ከእንስሳት በሽታ መከላከላቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል። የሰሜን ሸዋ ዞን የእንስሳት ሀብት ልማት ተጠሪ ጽህፈት ቤት በበኩሉ ለአርሶ አደሩ እንስሳት የክትባት አገልግሎት በመስጠት ከእንስሳቱ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግሯል። በዞኑ የቤት እንስሳትን ከተላላፊና ገዳይ በሽታዎች ቀድሞ ለመከላከል በተሰራው ሥራ ባለፉት አራት ወራት ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ እንስሳት ክትባት መሰጠቱንም ገልጸዋል። በተጠሪ ጽህፈት ቤቱ የእንስሳት በሽታ ቅኝት ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ዘላለም ይታየው ለኢዜአ እንደገለጹት ከተሰጡት ክትባቶች መካከልም አባሰንጋ፣ አባጎርባ፣ ጎረርሳና አጉረብርብ ይገኙበታል። በተጨማሪም የበግና የፍየል ፈጣጣ ደስታ መሰል በሽታዎች እንዲሁም የአፍሪካ የፈረሶች በሽታና የእብድ ውሻ በሽታዎች ይጠቀሳሉ። ክትባቱ የተሰጣቸው የቤት እንስሳት ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ477 ሺህ 892 ብልጫ አለው። ለዚህም ለእንስሳት ከትባት ቀድሞ ትኩረት መሰጠቱና የህብረተሰቡ ግንዛቤ እያደገ መምጣቱን በምክንያትነት ጠቅሰዋል። በሰሜን ሽዋ ዞን ከ4 ሚሊዮን በላይ የቤት እንስሳት ይኖራሉ ተብሎ እንደሚገመት ከተጠሪ ጽህፈት ቤቱ የተገኘውን መረጃ ጠቅሶ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም