የቅንጅትና የአመራር ቁርጠኝነት ማነስ ለህገ-ወጥ ንግድ መስፋፋት ምክንያት ሆኗል---የዘርፉ ባለድርሻ አካላት

67
ሀዋሳ ህዳር 23/2011 የቅንጅትና የአመራር ቁርጠኝነት ማነስ ለህገ- ወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት ምክንያት መሆኑን የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ገለጹ፡፡ የገቢዎች ሚኒስቴርና የፌደራል ፖሊስ በበኩላቸው ችግሩን ለመፍታት የተቀናጀ አደረጃጀት መጀመራቸውን አስታውቀዋል፡፡ የገቢዎች ሚኒስቴር ዛሬ በሀዋሳ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት ህገ-ወጥና ኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል ቅንጀታዊ አሰራርና የአመራር ቁርጠኝነትን ማስፈን እንደሚያስፈልግ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል ። የሲዳማ ዞን ንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ እንደገለፁት ወደ ዞናቸው ቀረጥ ሳይከፈልባቸው የሚገቡ ሞተር ሳይክሎች ንግድና ዝውውር እየተስፋፋ ነው። የመንጃ ፈቃድ ባላወጡ አሽከርካሪዎች የሰሌዳ ቁጥር በሌላቸው ሞተር ሳይክሎች ህገ-ወጥ ንግድ እንደሚኪያሄድ ተናግረዋል ። በህገወጥ የሞተር ሳይክሎች እንቅስቃሴ በሚከሰት አደጋ ለሰዎች ሞትና ንብረት ውድመት ምክንያት መሆኑን የገለፁት ኃላፊዋ የቁጥጥር ማነስ ድርጊቱን ለመከላከል ማነቆ መሆኑን ጠቁመዋል ። "የአመራሩ ቁርጠኝነት ማነስና አንዳንዴም በችግሩ መዘፈቅ ጉዳቱን የከፋ አድርጎታል" ያሉት ኃላፊዋ ድርጊቱን ለመከላከል የተቀናጀ ስራ ይጠይቃል" ብለዋል ። "ህገ -ወጥ ንግድ በልማታዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚና በኪራይ ሰብሳቢው መካከል የሚደረግ ትግል ነው" ያሉት ደግሞ የምዕራብ አርሲ ዞን ጸጥታ ጽህፈት ቤት ሃላፊ መቶ አለቃ ያሲን ገርጁ ናቸው፡፡ በዞናቸው ኩየራ ኬላ ላይ የገቢና ወጭ እቃዎችን በመቆጣጠር ክፍተት መኖሩን ጠቁመው ችግሩ ከኢኮኖሚ ባለፈ ለዜጎች ህይወት መጥፋት ምክንያት እየሆነ በመምጣቱን ተናግረዋል ። "በጉምሩክ አካባቢ የአገሪቱን ህብረ ብሄራዊነት ታሳቢ ያደረገ የአደረጃጀትና የአሰራር ለውጥ ያስፈልጋል" ብለዋል ። የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ኮማንደር ሂድር አቶም "በክልሉ የሚደረግ ህገ- ወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ ብሄርና ጎሳን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆነዋል" በክልሉ ከፍተኛ የሆነ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እንደሚከናወን የገለፁት ምክትል ኮሚሽነሩ ሽጉጦች፣ ክላሾችንኮቭ ጠመንጃዎች፣ የጦር ሜዳ መነጽሮች ጭምር በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን  ለአብነት ጠቅሰዋል ። "መሳሪያ አዘዋዋሪዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ህገ-ወጦች እንዳይጠፉና ድርጊቱ እንዳይቆም ምክንያት ሆኗል" ያሉት ምክትል ኮማንደሩ የህግ የበላይነትን በማስፈን ድርጊቱን መከላከል እንደሚገባ ጠቁመዋል። በህገ-ወጥ መንገድ ከሱዳን ወደ አገር ውስጥ ከሱዳን የሚገባ የዘይትና ስኳርን ጨምሮ የጎዳና ላይ ንግድ እየተበራከተ መሆኑን የገለፁት ኮማንደሩ ድርጊቱን ለመከላከል አመራር በቁርጠኝነትና የኃላፊነት ስሜት ሊኖር እንደሚገባ ጠቁመዋል። የፌደራል ገቢዎች ባለስልጣን ሚኒስትር ወይዘሮ አበበች አበቤ “በህገ- ወጥና ኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል ህዝቡን ያሳተፈ አገራዊ ንቅናቄ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡ የህገ- ወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ በአገር ላይ እያስከተለ ያለው ጉዳት እየጨመረ በመምጣቱ ድርጊቱን ለመከላከል ጉምሩክ በኮሚሽን ደረጃ እንዲቋቋም መደረጉን ተናግረዋል ። በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የሚገኙ የመንግስትና የህዝብ ሃብቶች ሲያዙ  ወንጀሎችን የመያዝና በህግ የማስጠየቁ ስራ ክፍተት ያለበት በመሆኑ ከፌደራል ፖሊስ ጋር የተቀናጀ ስራ መጀመሩን ጠቁመዋል ። “የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን በማዘመን ከእጅ ንኪክ ነጻ የማድረግና አገልግሎቱን ማሻሻል ትኩረት ሌላው ትኩረት ነው” ሲሉ ለተግባራዊነቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አደረጃጀቱን እየቀየረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፈንታ “በህገ-ወጥ መንገድ የሚገባ የመሳሪያ ዝውውር የአገሪቱን ሰላም ስጋት ውስጥ የሚጥል ነው” ብለዋል፡፡ መሳሪያዎቹ ለሽብር አገልግሎት እየዋሉ በመሆኑ ችግሩን መፍታት የሚያስችል አዲስ አደረጃጀት መፈጠሩን አቶ መላኩ አስታውቀዋል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም