ቅዱስ ጊዮርጊስ በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ድሉን አስመዘገበ

67
አዲስ አበባ ህዳር 23/2011 በ4ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስሁል ሽሬን 4ለ0 በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል። በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአቤል ያለው 2 ግቦች እንዲሁም በአሜ መሐመድ እና አምበሉ ምንተስኖት አዳነ ግቦች ነው ያሸነፈው። በጨዋታው ባለሜዳው ቅዱስ ጊዮርጊስ በኳስ ቁጥጥርና የግብ እድሎችን በመፍጠር ከተጋጣሚው ቡድን የተሻለ ነበር። በአንጻሩ እንግዳዎቹ ስሁል ሽሬዎቸ በአጭር የኳስ ቅብብል ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ቢያደርጉም በአጨራረስ ድክመት  ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። በክልል ከተሞች በተደረጉት ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ መቀሌ ሰብአ እንደርታን 1ለ0 አሸንፏል። አዳማ ከተማ ከሲዳማ ቡና ጋር ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ የተጠናቀቀ ሲሆን ፋሲል ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም ባህርዳር ከተማ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ያደረጉዋቸው ጨዋታዎቸ በተመሳሳይ 0 ለ0 ተጠናቀዋል። በፕሪሚየር ሊጉን ኢትዮጵያ ቡናና ሀዋሳ ከተማ በተመሳሳይ 7 ነጥብ በግብ ተበላልጠው በቅደም ተከተል 1ኛ እና 2ኛ ደረጃን የያዙ ሲሆን መቀሌ ሰብአ እንደርታ በ6 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።                          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም