አገልጋይ ሲቪል ሰርቫንት መፍጠር ያስፈልጋል ፤የውይይት ተሳታፊዎች

342
አዲስ አበባ ህዳር 23/2011 በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ለማሳካት ቅን አገልጋይ ሲቪል ሰርቫንት መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ። ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ጋር "ሁለንተናዊ ተሳትፎን በማጎልበት የተጀመረውን ለውጥ ከግብ ለማድረስ በቅንነት የሚያገለግል ፐብሊክ ሰርቪስ እንፈጥራለን" በሚል ርዕስ ላይ ዛሬ አወያይቷል። የውይይት መነሻ ጽሁፍ በማህበረሰብ ጤናና አመራር አማካሪው ዶክተር ኤርሲዶ ለንበቦ ቀርቧል። በጽሁፋቸው ኢትዮጵያ አሁን የጀመረችውን ለውጥ ከግብ ለማድረስ ህዝብን በቅንነት በማገልገል እርካታን መፍጠር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል። ለውጥ በግለሰብ፣ በአካባቢ እንዲሁም በተቋም ማምጣት አስፈላጊ መሆኑን በመጠቆም በተላይ በግለሰብ ለውጥ ላይ ትኩረት ሰጥተዋል። ዶክተር ኤርሲዶ አንድ ሲቪል ሰርቫንት በተሰማራበት ሙያ ለእያንዳንዱ ግለሰብ በሚሰጠው አገልግሎት ኢትዮጵያን እንዳገለገለ መቁጠር አለበት ሲሉም የግለሰብ ለውጥን አብራርተዋል። ለአብነትም የመዝገብ ቤት ሰራተኛ ኢትዮጵያ መዝገቡ መሆኗን በማሰብ መረጃዎችን አደራጅቶ በመያዝ ህዝብን በፍጥነትና በቅንነት ማገልገል ይችላል ሲሉም በምሳሌ አጠናክረዋል። በመሆኑም አሁን በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ለማሳካት የህዝብ አገልጋይ ግለሰብ ለውጥ ወሳኝ ነው ሲሉ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ህዝብ በሚያገኘው አገልግሎት እንዲረካ ቅንነት ወሳኝ መሆኑን በመስማማት ደሞዝና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ግን መስተካከል እንዳለባቸው ጠይቀዋል። ለሲቪል ሰርቫንቱ የሚከፈለው ደሞዝ ዝቅተኛ መሆን በሰዓት ስራው ላይ እንዳይገኝ፣ ህዝብን በቅንነት እንዳያገለግል፣ ከእኛ (ከኢትዮጵያ) ይልቅ በግላዊነት ላይ እንዲያተኩር አድርጎታል ሲሉም በአስተያየታቸው አንስተዋል። የአዲስ አበባ  ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ነጻነት ዳባ በበኩላቸው በከተማዋ የተጀመሩ ለውጦችን ለማሳካት የሲቪል ሰርቫንቱ ቅን አገልግሎት ወሳኝ ነው ብለዋል። ለውጥን ከህዝብ ፍላጎትና ጥቅም ጋር በማስተሳሰር አገልግሎትን ለህዝብ በመስጠት ኢትዮጵያን ከፍ እናድርግ ሲሉም ተደምጠዋል። በመድረኩ ከከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ቢሮ ሃላፊዎችና ተወካዮች፣ የሴቶችና ወጣት ማህበራት፣ ህግ አውጪዎችና ሌሎችም ተገኝተዋል። በኢትዮጵያ ካሉት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የመንግስት ሰራተኞች ከ100 ሺህ በላይ በአዲስ አበባ የሚገኙ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም