ለአርሶ አደሩ ምርታማነት ማደግ መልካም ተሞክሮዎችን መቀመር ይገባል---ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

121
ደብረብርሀን  ህዳር 23/2011 የአርሶ አደሩን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ መልካም ተሞክሮዎችን መቀመርና ማስፋት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሰቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሞረትና ጅሩ ወረዳ ኩሳየ ቀበሌ ተገኝተው የአርሶ አደሮችን ማሳ ጎብኝተዋል ። ዶክተር አብይ በወቅቱ እንደገለፁት የሀገሪቱን የሰብል ምርታማነት ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን በአስተማማኝነት ለማረጋገጥ የተሻሻሉ አሰራሮች ሊተገበሩ ይገባል። "ሰብልን በኩታ ገጠም  ማሳ በማልማት የአርሶ አደሩን የእርስ በእርስ የመማማር ባህል በማጎልበት ምርታማነትን በጥፍ በመጨመር ለኢንዱስትሪዎች ግብአትና ለውጭ ገበያ የሚሆን ጥራቱን የጠበቀ ምርት ማቅረብ ግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ነን" ብለዋል። "ሀገራችን ዓመቱን ሙሉ ማምረት የሚያስችል ተስማሚ የአየር ፀባይ ባለቤት ብትሆንም አርሶ አደሩን በበቂ መጠን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ማድረግ ባለመቻሉ ከውጭ ሀገራት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የስንዴ ምርት እያስገባን እንገኛለን" ሲሉም ተናግረዋል ። ወጣቱን በማደራጀትና አርሶ አደሩን በተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ በማድረግ በኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅጽኖ እያደሰረ ያለውን የሰብል አቅርቦት እጥረት መፍታት እንደሚገባ ጠቁመዋል ። እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ገለጻ የግብርና ምርታማነትና ጥራትን ለማሻሻል መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ። የኢፌድሪ ግብርና ሚኒስትር አቶ ኡመር ሁሴን በበኩላቸው "ሰሜን ሽዋ ዞን የስንዴ አብቃይ በመሆኑ ለሌሎች አካበቢዎች ሰፊ ልምድና ተሞክሮ የሚቀሰምበትና የሚቀመርበት ነው " ብለዋል ። በዞኑ የኩታ ገጠም ሰብል አመራረትን ለማስፋፋት በተሰራ ስራ ውጤት እየተመዘገበ መምጣቱን ተናግረዋል። በዘርፍ እየታየ ያለውን አበረታች ለውጥ ለማስቀጠል በአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ጥልቀት ያለው ስልጠና በመስጠት ተሞክሮውን ወደ ሌሎች አካባቢዎች የማስፋፋት ስራ እንደሚሰራ አመላክተዋል ። በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መግርሳ በዞኑ የተመለከቱት የአርሶ አደሮች በኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ የመጠቀም ልምድ በተሞክሮነት ሊወሰድ የሚችል መሆኑን ተናግረዋል። "በተለይም ውሃ የሚተኛበትን የጥቁር አፈር መሬት በቴክኖሎጂ በማንጣፈፍ ወደ ምርታማነት እንዲገባ መደረጉ የተሻለ ልምድና ተሞክሮ የተገኘበት ነው" ያሉት ፕሬዝዳንቱ የክልላቸው አርሶ አደሮች ልምዱን እንዲወስዱ እንደሚደረግ አመላክተዋል ። "በዞኑ በመኽር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ዘር ከተሸፈነው ግማሽ ሚሊዮን ሄክታር ማሳ ውስጥ 81 ሺህ ሄክታሩ በኩታ ገጠም የለማ ነው" ያሉት ደግሞ የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት ሃይሌ ናቸው። በኩታ ገጠም ከለማው ውስጥ 46ሺህ 605 ሄክታር የሚሆነው ስንዴ መሆኑን የገለፁት ኃላፊዋ "ከምርት ወቅቱ 3 ሚሊዮን ኩንታል ጥራቱን የጠበቀ የስንዴ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል " ብለዋል ። "ከዚህ ቀደም በኩታ ገጠም ከሚለማው ከአንድ ሄክታር ማሳ ይገኝ የነበረውን 27 ኩንታል የስንዴ ምርት ወደ 60 ኩንታል ማሳደግ ተችሏል"ሲሉ ኃላፊዋ አስታውቀዋል ። በሞረትና ጅሩ ወረዳ የኩሳየ ቀበሌ አርሶ አደር ወርቁ እሸቴ በመኽር ወቅት አንድ ሄክታር ኩታ ገጠም ማሳ ላይ ከዘሩት ስንዴ ከ50 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል። "የምርት ማጨጃና መውቂያ ማሽን ቢቀርብልን የበለጠ ውጤታማ እንሆናለን " ያሉት ደግሞ ሌላው የቀበሌው አርሶ አደር ዳምጠው በቀለ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከማሳ ጉብኝት በኋላ ከአርሶ አደሮች ጋር የተወያዩ ሲሆን የአካበቢው ማህበረሰብ ባህላዊ ልብስ በመሆን የሚታወቀውን በርኖስ እንዲሁም የጅሩ ሰንጋና ሌሎች ቁሳቁሶች በስጠታ ተበርክቶላቸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም