በመንግስት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ለረዥም ጊዜ የተከማቸ ንብረት ተወገደ

92
አዲስ አበባ ህዳር 23/2011 በመንግስት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ለረዥም ጊዜ የተከማቸ ንብረት በሽያጭ መወገዱን የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አስታወቀ። ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ ለረዥም ዓመታት በመንግስት ባለበጀት ተቋማት የተከማቸ ንብረትን በመንግስት ግዥና ንብረት አገልግሎት ብቻ ለማስወገድ ከአቅም በላይ የነበረበት ጊዜ እንደነበረም የተናገሩት የድርጅቱ  ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ይገዙ ዳባ ናቸው ። ይህን ችግር ለመፍታትና ብክነትን ለማቃለል የጥቅል ሽያጭ ዋጋቸው ከ100 ሺህ ብር በላይ የሆኑ ንብረቶችን ጨምሮ ተቋማቱ ያላቸውን ማንኛውንም ያገለገለ ንብረት በሽያጭ እንዲያስወግዱ ውክልና ተሰጥቶ እንደነበርም ገልፀዋል። እንደ አቶ ይገዙ ገለፃ ተቋማቱ የነበራቸውን ውዝፍ ንብረት በሽያጭ በማስወገዳቸው  በየተቋማቱ ለረዥም ዓመት የተቀመጡ የንብረት ብክነት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መፍታት ተችሏል። ለተቋማቱ ተሰጥቶ የነበረው የውክልና ጊዜ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓም መጠናቀቁንና ባለፉት ሶስት ወራት በሽያጭ ንብረት ለማስወገድ ባከናወነው ተግባር ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ማስገባቱን ነው ያሳወቀው። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ከአሁን በፊት በርካታ ክምችት በነበረባቸው በኢትዮጵያ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ እና በግብርና ሚኒስቴር ተዘዋውሮ ያናገረ ሲሆን ከ80 በመቶ በላይ ማስወገዳቸውን ተናግረዋል። አቶ ግዛቸው አሰግድ በግብርና ሚኒስቴር የንብረት ስራ አመራር አገልግሎት ሃላፊ እንዳሉት "በዕኛ ግምገማ 80 በመቶ አስወግደናል ብለን ነው ያሰብነው    ምክነያቱም እድሉን በደንብ ነው የተጠቀምነው” ለረዥም ጊዜ የተከማቸ ንብረትን   ሰማኒያ አምስት  ፐርሰንት ማስወገዳቸውንና  የሚቀር ስራ መኖሩን የጠቆሙት ደግሞ በኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ታምሩ መርሻ ናቸው፡፡  ከዚህ በተጨማሪ በሁለቱም ተቋማት ጨረታቸው በሂደት ላይ ያሉ ተሽከርካሪዎችና አንዳንድ ንብረቶች መኖራቸውን በተዘዋወርንበት ወቅት ለማወቅ ተችሏል።  ከዚህ በኋላ በሚኖረው የስራ ጊዜ በመንግስት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ያገለገሉ ንብረቶች እንዳይከማቹና ንብረትን በወቅቱና በአግባቡ የማስወገዱ ልምድ እንዲዳብር ከተቋማቱ ጋር በየሦስት ወሩ የምክክር መድረክ እንደሚደረግም ከመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታክል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም