መገናኛ ብዙሃን የተሻለ ነጻነት አግኝተው እየሰሩ ቢሆንም የፋይናንስ እጥረትና የአቅም ክፍተት አለባቸው - ምሁራንና የሚዲያ አመራሮች

93
ህዳር 23/2011 ከስምንት ወራት ወዲህ መንግሥት እየወሰደ ባለው የለውጥ እርምጃዎች መገናኛ ብዙሃን የተሻለ ነጻነት አግኝተው እየሰሩ ቢሆንም የፋይናንስ እጥረትና  የአቅም ክፍተት እንዳለባቸው የዘርፉ ምሁራንና  አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን አመራሮች ተናገሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ47 በላይ የግል የህትመትና የብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን ፈቃድ ተሰጥቷቸው በስራ ላይ መሆናቸውን  የብሮድካስት ባለስልጣን አስታውቋል። የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙሃን ባገኙት ነፃነት የተለያዩ ሀሳቦችን በመተቸትና የምርመራ ዘገባዎችን በመስራት ላይ መሆናቸውን  ነው ያነጋገርናቸው ምሁራን  የገለጹት። የግል የህትመት ሚዲያው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያንሰራራ መምጣቱ መልካም ቢሆንም፤ የግል ስሜት የተቀላቀለባቸውን ዘገባዎች እያየን ነው ያሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ምሁር ዶክተር ተሻገር ሺፈራው ናቸው። በሃላፊነት ስሜት አለመሥራት፣ ህዝባዊ ውግንና አለመኖር፣ ሚዛናዊ ያልሆኑ ዘገባዎች አሁንም በግል መገናኛ ብዙሃን እየተንጸባረቁ መሆኑን ነው ምሁሩ ያነሱት። “የግል መገናኛ ብዙሃን ከዚህ ቀደም መረጃ እንከለከላለን ይሉ ነበር፤ አሁን ተቋማት በራቸውን ክፍት እያደረጉ ነው፤ ይህን አጋጣሚ ለሚዛናዊ ዘገባ ማዋል ይገባቸዋል” ነው ያሉት። በሀገሪቱ የሚታዩ የብሔርና የአንድነት ፖለቲካ  የግል መገናኛ ብዙሃኑን ወደተዋጊ ጋዜጠኝነት ሚና እንደከተታቸውም ነው ዶክተር ተሻገር  ያነሱት። በመገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ ዘገባዎችን ለመገምገምና የጋዜጠኞችን አዘጋገብ ለመፈተሽ ነጻ ማህበራትና ምክር ቤቶችን ማቋቋም እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ምክትል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ሄኖክ ስዩም የግል የህትመት መገናኛ ብዙሃንን ለማጠናከር የወረቀትና የማተሚያ ድጋፎችን ከመንግሥት መገናኛ ብዙሃን እኩል የሚያገኙበት እድል  ሊፈጠርላቸው እንደሚገባ ነው የሚናገሩት፡፡ በኢትዮጵያ “የሚዲያ ኢምፓየር” መፈጠር አለበት ያሉት የአሃዱ ኤፍ.ኤም ሬዲዮ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥበቡ በለጠ ከኬንያ፣ ከኡጋንዳና ከደቡብ አፍሪካ ትምህርት መውሰድ እንደሚገባም  ተናግረዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ የአንድ መፅሄት ከፍተኛው ህትመት 10 ሺህ ኮፒ መሆኑን የገለፁት አቶ ጥበቡ የመገናኛ ብዙሃኑን የስርጭት መጠናቸውን ለማሳደግ የወረቀት ዋጋ መቀነስ አለበት ይላሉ፡፡ የሸገር ታይምስ መጽሄት ዋና አዘጋጅ ሰለሞን ታደሰ በበኩላቸው  የስርጭት መጠን ውስን መሆን፣ የህትመት ዋጋ እየጨመረ መምጣት፣ ከዚህ በፊት የነበረው በየክልሎች እንዳይሰራጩ የማድረግ ክልከላ አሁንም ስጋት መሆኑን ገልጸው አሰራሩ ተሻሽሎ ጋዜጦችና መጽሄቶች በመላው ሀገሪቱ  ተደራሽ እንዲሆኑ መስራት ይገባል ነው ያሉት። ተዘግተው የነበሩ የህትመት ሚዲያዎች ወደ ገበያው እየተመለሱ መሆኑ በጎ ጅምር ነው ያሉት በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ሚዲያ ኮሙዩኒኬሽን መምህር አየለ አዲስ፤ የተወሰኑ መገናኛ ብዘሃን በህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ላይ ያተኮሩ የምርመራ ዘገባዎችን በማቅረብ ሀገርን የማዳን ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረግ መጀመራቸውንም  ተናግረዋል። ሙያውን ሳይንሳዊ በማድረግ እና መፍትሄ አቀፍ ዘገባን በመጠቀም ረገድ ክፍተት ያለባቸው መገናኛ ብዙሃን መኖራቸውንም መምህር አየለ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ47 በላይ የግል መገናኛ ብዙሃን ስራ ላይ እንደሚገኙ ነው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ገብረጊዮርጊስ አብረሃ የተናገሩት፡፡ በሀገሪቱ 24 የግል የህትመት መገናኛ ብዙሃን በስርጭት ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ከነዚህ መካከል 11ዱ ጋዜጦች ሲሆኑ 13ቱ ደግሞ መጽሄቶች  ናቸው ብለዋል፡፡ በጥቅምት 2011 ዓ.ም ብቻ አራት አዲስ የግል ህትመት መገናኛ ብዙሃን ተመዝግበው ሥራ መጀመራቸውንም ነው የገለፁት፡፡ የሥራ ፈቃድ ከወሰዱ 12 የግል ሬዲዮ ጣቢያዎች ዘጠኙ ስርጭት መጀመራቸውና  ሶስቱ  በዝግጅት ላይ መሆናቸውን የተናገሩት  አቶ ገብረጊዮርጊስ ፈቃድ ከተሰጣቸው 16 የግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች  11ዱ በመደበኛ ስርጭት ቀሪዎቹ በሙከራ ስርጭትና በዝግጅት ላይ  ናቸው ብለዋል፡፡ የሀበሻ ወግ መፅሄት ማኔጂንግ ዳይሬክተር የአይኔአበባ ይግዛው አብዛኛዎቹ የግል የህትመት መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞችና ጸሃፊዎች የአቅም ክፍተት እንዳለባቸው ይገልጻሉ። ከዚህ ቀደም ተዘግተው የነበሩ አዳዲስ ጣቢያች፣ ጋዜጦችና መጽሄቶች ወደ ምህዳሩ መምጣታቸው ተስፋን ቢያሳይም የፋይናንስ ውስንነት ያለባቸው መሆኑ ስጋት እንደሚፈጥርም ነው  ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ የተናገሩት፡፡ የግል ሚዲያዎች በፋይናንስ አቅም የተዳከመ በመሆኑ በገንዘብ ተጠልፈው የአንድ ፖለቲካ ድርጅት ልሳን  እንዳይሆኑ  ስጋት  እንዳላቸው ጨምረው ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ጠቃሚና የምርመራ ስራዎችን ለማበረታታት የፋይናንስ ውስንነታቸውን የሚፈቱበትን መንገድ በማመቻቸት ሊያጠናክራቸው ይገባል  ያሉት ደግሞ በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ሚዲያ ኮምዩኒኬሽን መምህር አየለ አዲስ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ የግል የመገናኛ ብዘሃን አሁን ያገኙት ተስፋ እንዳይመክን መሥራት እንደሚገባቸው ለምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ መናገራቸው ይታወሳል። የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት፣ ያለባቸው የፋይናንስ እጥረት እንዲፈታ፣ የማስታወቂያ ገቢን በፍትሃዊነት እንዲጠቀሙ መንግሥት፣ ህዝቡና መገናኛ ብዘሃኑ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡ ከ2001 እስክ 2011 ዓ.ም ጥቅምት ወር ድረስ  417 የግል የህትመት መገናኛ ብዙሃን ስርጭት ለመጀመር ቢመዘገቡም በርካታዎች ከገበያ መውጣታቸው የብሮድካስት ባለስልጣን የተገኘ መረጃ  ያሳያል። በኢትዮጵያ ከሽግግር ቻርተሩ ጀምሮ ከ2 ሺህ የማያንሱ የህትመት መገናኛ ብዘሃን የነበሩ ቢሆንም አብዛኛዎቹ በተለያዩ ምክንያቶች ከገበያ እንደወጡም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ሀገራዊ ለውጡ ሰዎች ሀሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹ እድል በመፈጠሩ በመንግሥት ታግደው የነበሩ ከ264 በላይ መገናኛ ብዘሃንና ብሎጎች ተፈቅዶላቸው አገልግሎት ላይ መሆናቸውን ነው ከጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት የተገኘ  መረጃ የሚያሳየው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም