የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን ህይወት ለመቀየር የአሰራር ለውጥ እየተደረገ ነው--ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ

104
አዲስ አበባ ህዳር 23/2011 በአዲስ አበባ ከተማ የልማት ተነሺ የሆኑ አርሶ አደሮችን ህይወት በዘላቂነት ለመቀየር የአሰራር ለውጥ እያደረገ መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር ገለጸ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የልማት ተነሺ ከሆኑ የከተማዋ አርሶ አደሮች ጋር በቀጣይ ህይወታቸውን ማሻሻል በሚችሉበት ጉዳይ ላይ ውይይት አድርገዋል። አርሶ አደሮቹ "ለልማት ነው እየተባለ ከርስታችን ስንፈናቀል፤ የጋራ ልማት ነው ብለን ብንቀበለውም ተገቢውን ካሳና ድጋፍ እያገኘን አይደለም" ብለዋል። አርሶ አደሮቹ ምትክ ተብሎ የተሰጣቸው ቦታ እንደ መብራት፣ ውሃና መንገድ ያሉ የመሰረተ ልማት አውታሮች ያልተዘረጉበትና ከማህበራዊ ህይወታቸው የተገለሉበት መሆኑን አስረድተዋል። "የካሳ ክፍያ በየዓመቱ መሻሻል አለበት የሚል አሰራር ቢኖርም መመሪያው ተግባራዊ እየተደረገ አይደለም፤ ክፍያውም ዝቅተኛ በመሆኑ ህይወታችንን በዘላቂነት መምራት አልቻልንም" ብለዋል ተፈናቃዮቹ። የግንባታ ፈቃድ አሰጣጡ ቢሮክራሲው የበዛ ከመሆኑም በላይ፣ ዘመድ ወይም ገንዘብ ከሌለ አገልግሎቱን ማግኘት ከባድ መሆኑን ጠቁመዋል። ለቤት መስሪያ ምትክ ቦታ 500 ካሬ ሜትር መሬት የተሰጠው ግማሹን በብሎኬት ካልሰራ ፈቃድ እንዳያገኝ የሚከለክለው መመሪያም "መኖሪያ ቤት አንኳን እንዳይኖረን አድርጎናል" ይላሉ። ምክንያቱ ደግሞ ከ130 እስከ 150 ሺህ ብር ካሳ የተሰጠው አርሶ አደር ግማሹን ወይንም 250 ካሬ ሜትር መሬት "በብሎኬት መስራት የሚችልበት አቅም የለውም ነው" የሚሉት። አካባቢው መሰረተ ልማት ያልተዘረጋበትና ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል ሁኔታ የሌለበት በመሆኑ "አብዛኞቹ ወጣቶች ለሱስ ተጋላጭ ሆነዋል" ብለዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ዛሬ የሚያነሱት ጥያቄ "ትክክለኛና በመንግስት የተፈጠረ ስህተት" መሆኑን ገልጸዋል። የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ስራውን በአግባቡ እያከናወነ ባለመሆኑ እንደገና ለማደራጀትም ስራው ተጀምሯል ብለዋል። ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የሚለው ቀርቶ የከተማ ግብርና ቢሮ አርሶ አደሮች በከተማ ግብርና ህይወታቸውን በዘላቂነት መምራት የሚችሉበት አሰራር ይፈጠራልም ብለዋል። ከወረዳ ጀምሮ እሰከ ከተማ ባለው መዋቅርም በአርሶ አደሮች ላይ መጉላላት የሚፈጥሩ ባለሙያዎች ካሉ "ከወዲሁ ቦታቸውን እንዲይዙ ይደረጋሉ" ነው ያሉት። በከተማ አስተዳደሩ በኩል ያሉ የአሰራር፣ የመመሪያና የህግ ክፍተቶችም እየተፈተሹ ማሻሻያ ይደረግባቸዋል ብለዋል። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ "የተፈጠረው የትናንቱ ስህተት አይደገምም" ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ አርሶ አደሮች ከቤተሰቦቻቸው ጋር በአንድ አካባቢ አብረው የሚኖሩበት አሰራር ይፈጠራል ብለዋል፤ የለገሃርን የተቀናጀ መንደር ግንባታ በአብነት በመጥቀስ። በልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ስም ሀሰተኛ ማስረጃ ይዘው የሚመጡ አካላት እንዳሉ ጠቅሰው፤ ህገ ወጥነትን በመካላከል ከጎናችን እንድትሆኑ ሲሉም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም