የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ

104
አዲስ አበባ ህዳር 23/2011 የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች አንደኛ ዲቪዚዮን ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ። 12 ክለቦችን በሚያሳትፈው ፕሪሚየር ሊግ ትናንት በሁለተኛ ሳምንት መርሃ-ግብር ሶስት ጨዋታዎች መካሄዳቸው ይታወቃል። ዛሬም በክልል ከተሞች ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ። በአሰላ አረንጓዴ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ በመጀመሪያ ጨዋታቸው ከሜዳቸው ውጪ በሃዋሳ ከተማ 5 ለ 0 በሆነ ውጤት የተሸነፉ ሲሆን በአንጻሩ አዲስ አበባ ከተማ በመጀመሪያ ጨዋታው ጥረት ኮርፖሬትን ማሸነፉ ይታወሳል። ጨዋታው ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ በሊጉ የመጀመሪያ ድሉን ለማስመዝገብ አዲስ አበባ ከተማ የማሸነፍ ጉዞውን ለመቀጠል የሚያደርጉት ነው። ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ የሚያጫውታቸው ተጫዋቾች በአካዳሚው ሰልጥነው የተመረቁ ታዳጊዎች ናቸው። በአርባምንጭ ስታዲየም አርባምንጭ ከተማ ከጌዲኦ ዲላ ጋር ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ይጫወታሉ። አርባምንጭ በመጀመሪያ ሳምንት መርሃ-ግብሩ ከሜዳው ውጪ ቅዱስ ጊዮርጊስን ያሸነፈ ሲሆን ጌዲኦ ዲላ ድሬዳዋ ከተማን አሸንፏል። ሁለቱ ክለቦች በሊጉ ጥሩ ግስጋሴ ለማድረግ የዛሬውን ጨዋታቸውን ለማሸነፍ ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ትናንት በተደረጉ ጨዋታዎች ጥረት ኮርፖሬት ኢትዮ ኤሌትሪክን 1 ለ 0 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅዱስ ጊዮርጊስን 3 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል። አዳማ ከተማ ከሃዋሳ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል። በሁለተኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ-ግብር ህዳር 16 ቀን 2011 ዓ.ም በተደረገ ጨዋታ መከላከያ ድሬዳዋ ከተማን 3 ለ 2 በሆነ ውጤት ማሸነፉ የሚታወስ ነው። የኢትዮጵያ ሴቶች አንደኛ ዲቪዚዮን ፕሪሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በስድስት ነጥብ ሲመራ ሃዋሳ ከተማና አዳማ ከተማ በተመሳሳይ አራት ነጥብ ግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 11ኛ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ 12ኛ ደረጃን በመያዝ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም