የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይካሄዳሉ

62
አዲስ አበባ ህዳር 23/2011 የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት መርሃ ግብር በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በሚካሄዱ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይካሄዳሉ። በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰዓት ፈረሰኞቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከ ስሑል ሽረ ጋር ይጫወታሉ። ገና ከጅምሩ በተለያዩ ምክንያቶች እየተቋረጠ ወጥነት በጎደለው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ እስካሁን አንድ ጨዋታ ብቻ ነው ያደረገው። በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ፖርቹጋላዊውን አሰልጣኝ ማኑኤል ቫዝ ፒንቶን ካሰናበተ በኃላ በምክትል አሰልጣኙ ዘሪሁን ሸንገታ መሪነት ሊጉን የጀመረው ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያውን ጨዋታ በባህር ዳር ከተማ 1 ለ 0 መሸነፉ የሚታወስ ነው። በደረጃ ሰንጠረዡም 15ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ክለቡ በአሁኑ ሰዓት እንግሊዛዊውን አሰልጣኝ ጆን ስቲዋርት ሃልን በአሰልጣኝነት የቀጠረ ሲሆን አሰልጣኙም ክለቡን ከተረከቡ በኋላ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ዛሬ ያደርጋሉ። አዲስ አዳጊው ስሑል ሽረ እስካሁን ሁለት ጨዋታዎቸን ተጫውቶ ሁለቱንም አቻ በመውጣት በሁለት ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚደረገው ጨዋታ ክለቦቹ በፕሪሚየር ሊጉ የሚያደርጉት የመጀመሪያ ጨዋታቸውም ይሆናል። በአራተኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር በክልል ከተሞች አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ከሲዳማ ቡና፣በጎንደር ስታዲየም ፋሲል ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና፣በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ባህርዳር ከተማ ከሃዋሳ ከተማ፣በወላይታ ሶዶ ስታዲየም ወላይታ ድቻ ከመቐለ ሰብአ እንደርታ ጋር በተመሳሳይ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። ትናንት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በተደረገ አንድ ጨዋታም ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ በኤፍሬም አሻሞ ብቸኛ ጎል ደቡብ ፖሊስን 1 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል። ጅማ አባ ጅፋር ከድሬዳዋ ከተማና ደደቢት ከመከላከያ ሊያደርጉት የነበረው የአራተኛ ሳምንት ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋርና መከላከያ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግና በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ በቅደም ተከተል የቅድመ ማጣሪያ ባለባቸው የመልስ ጨዋታ ምከንያት ለሌላ ጊዜ ተራዝሟል። እስካሁን በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በተደረጉ ጨዋታዎች መቐለ ሰብአ እንደርታ፣ኢትዮጵያ ቡናና ሃዋሳ ከተማ በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል። ድሬዳዋ ከተማ፣ቅዱስ ጊዮርጊስና ደደቢት ከ14ኛ እስከ 16ኛ ደረጃ ያለውን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም