ወደ ነዳጅ ምርትና ሽያጭ ለመግባት እስከ ሶስት ዓመት ይጠይቃል

2145

አዲስ አበባ ህዳር 23/2011 ኢትዮጵያ ወደ ነዳጅ ሃብት ምርት ገብታ ተጠቃሚ ለመሆን እስከ ሶስት ዓመት እንደሚፈጅባት የማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የነዳጅ ፈቃድና አስተዳደር ዳይሬክተር ዶክተር ቀፀላ ታደሰ በአሁኑ ወቅት ነዳጅ በተገኘባቸው አካባቢዎች ተጨማሪ ጥናት በማድረግና በሌሎች ቦታዎች በመፈለግ ደረጃ ላይ ነን ብለዋል።

ቀደም ሲል በሶማሌ ክልል ኦጋዴን አካባቢ ከ4 ነጥብ 7 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ በላይ የተገኘ ቢሆንም አሁን ያለበት ደረጃ ለምን አይነት አገልግሎት ቢውል እንደሚያዋጣና ለማንና እንዴት መሸጥ እንዳለበት ጥናት በማድረግ ላይ ነን ሲሉ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

አሁን ከተቆፈረው ጥልቅ ጉድጓድ በተጨማሪ ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ጉድጓዶችና ሌሎች መሰረተ-ልማቶች እንደሚያስፈልጉና ይህም ቢያንስ እስከ ሶስት ዓመት እንደሚወስድ አስታውቀዋል።

ከዚህ በተጨማረም እስካሁን በተደረገው አሰሳ በአገሪቱ አምስት አካባቢዎች ተለይተው የተለያዩ የነዳጅ ጥናት አድራጊ ኩባንያዎች በብሎክ ተከፋፍለው እየሰሩበት ነው ብለዋል።

ከነዚህም ውስጥ ሶማሌ ክልል ኦጋዴን፣ ስምጥ ሸለቆ አካባቢ፣ እንዲሁም መቀሌ፣ መተማ፣ ጋምቤላ የሚጠቀሱ ናቸው።

በተያያዘ ዜና በደቡብ ወሎ ለገሃዲ ወረዳ ታየ የተባለው የነዳጅ ፍልቅታ ነዳጅ መሆኑ የተረጋገጠ ቢሆንም ያለው ክምችት መጠንና ትክክለኛ የክምችቱ አካባቢ የመለያ ጥናት ያስፈልገዋል ብለዋል።

ቀደም ሲል አንድ ኩባንያ በዚህ አካባቢ ጥናት ሲያደርግ መቆየቱንና ካለው የጥቁር አለት ንብርብርና የመሬቱ ተፈጥሮ አኳያ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑ ገንዘብ አጥሮት ማቋረጡንም አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት ከሌላ አቅም ካለው ኩባንያ ጋር በመደራደር ላይ ነን ያሉት ዳይሬክተሩ ከስምምነት ላይ ሲደረስ በአካባቢው ላይ የሚደረገው የጥናት ስራ የሚቀጥል ይሆናል ነው ያሉት።

የሚወጣውን ነዳጅ ለገበያ ለማዋል የሚያስፈልጉ የመሰረተ-ልማት ስራዎች፣ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ መቅበሪያ አካባቢዎችን የማጥናት፣ የወደብ አጠቃቀምና ሌሎች ስራዎችን በተመለከተም በሂደት ላይ ነው ብለዋል።