በኢትዮጵያ በሙከራ ደረጃ ባዮ ዲዝል ማምረት ሊጀመር ነው

1861

አዲስ አበባ ህዳር 23/2011 በኢትዮጵያ በሙከራ ደረጃ ባዮዲዝል ማምረት ሊጀመር ነው።

ኤ.ፒ.አይ የታዳሽ ሃይል ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የባዮ ዲዝሉን ምርት ሊጀምር መሆኑን አስመልክቶ ያዘጋጀው የማሳወቂያ መርሃ ግብር ትናንት ማምሻውን በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ባዮ ዲዝል እንደ መደበኛው ዲዝል ከድፍድፍ ነዳጅ ዘይት የሚገኝ ሳይሆን ከእጽዋትና ከእንስሳት ተዋጽኦ (ዘይትና ሞራ) የሚመረት የዲዝል አይነት ነው።

የማህበሩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ማርቆስ ቢተው የባዮ ዲዝል ምርቱ በኢትዮጵያ በሙከራ ደረጃ መመረት የሚጀምረው በአዳማ ኢንዱስትሪ ዞን ለማሳያ በሚል በተተከለው የባዮ ዲዝል ማጣሪያ ጣቢያ እንደሆነ ገልጸዋል።

በማጣሪያ ጣቢያው በቀን 12 ሺህ ሊትር ባዮ ዲዝል ለማምረት እቅድ መያዙንም ተናግረዋል።

ኩባንያው ምርቱም ለመጀመር ከገንዘብ ሚኒስቴር የፋይናንስ ዋስትና ደብዳቤና ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ለባዮ ዲዝል ምርቱ ደረጃ አሰጥቶ የማጽደቅ ስራ ብቻ እንደሚቀረው ጠቅሰዋል።

ሁለቱ ስራዎች በጥቂት ጊዜያት ከተጠናቀቁ በኋላ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሙከራ ደረጃ ባዮ ዲዝል ማምረት እንደሚጀመርም አመልክተዋል።

ከሙከራ ምርቱ በኋላ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ  የሚጠናቀቅ በ25 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በአዳማ ኢንዱስትሪ ዞን የባዮ ዲዝል ማቀነባበሪያና ማምረቻ ፋብሪካ እንደሚገነባም ነው አቶ ማርቆስ ያስረዱት።

ፋብሪካው ስራ ሲጀምርም በቀን 200 ሺህ ሊትር ባዮ ዲዝል ለማምረት እቅድ ተይዟል ብለዋል።

ኤ.ፒ.አይ የታዳሽ ሃይል ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እስከ 2017 ዓ.ም የአዳማውን ጨምሮ በኢትዮጵያ 10 የባዮ ዲዝል ማቀነባበሪያና ማምረቻ ፋብሪካዎችን ለመግንባት እቅድ መያዙንና ለዚህም 250 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

አስሩ ፋብሪካዎች በጋራ በየዓመቱ 730 ሚሊዮን ሊትር ባዮ ዲዝል ያመርታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል በደን ምንጠራ፣ በአፈር መሸርሸርና በዝናብ እጥረት የተለዩ ቦታዎች ለባዮ ዲዝል ግብአት በ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ጃትሮፋ (የጉሎ ዘይት ተክል) ተተክሎ ለምርት መድረሱንም አመልክተዋል።

ባዮ ዲዝል ከእጽዋትና ከእንስሳት ተዋጽኦ (ዘይትና ሞራ) የሚመረት በመሆኑም በከባቢ ላይ ተጽእኖ እንደማያሳድርም በጥናት መረጋገጡን ተናግረዋል።

ለአርሶ አደሮችም በባዮ ዲዝል ዙሪያ በተለያዩ ጊዜያት ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መሰራቱንም አውስተዋል።

የባዮ ዲዝል ምርቱም ለኤሌትሪክ ሃይል እንደሚውልና የታዳሽ ሃይል ምንጭ በመሆኑም ኢትዮጵያ የቅሪተ አካል ናፍጣን( ፎሲል ፊዩል) በመተካት ለቅሪተ አካል ናፍጣ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ አድና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታም ማግኘት አንደምትችል አስረድተዋል።

በማሳወቂያ መርሃ ግብሩ ላይ ባዮ ዲዝልን አስመልክቶ የዘርፉ ባለሙያዎች ሰፋ ያለ ገለጻ አቅርበዋል።

በመርሃ ግብሩ ወቅት የኤ.ፒ.አይ የታዳሽ ሃይል ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርና ዳሽን ባንክ “አሞሌ” የተሰኘ የዲጂታል መገበያያ የባዮ ዲዝል ግብአት የሚሆኑ ምርቶችና አገልግሎቶች ለሚያቀርቡ አርሶ አደሮች ገንዘባቸውን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማግኘት የሚያስችል ስምምነትም ተፈራረመዋል።

በስምምነቱ መሰረት ከ500 ሺህ በላይ የሚሆኑት አርሶ አደሮች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ተገልጿል።

ባዮ ዲዝል ’’ ጃትሮፋ ፣ ጉሎ ፣ አኩሪ አተር ፣ፖንጋሚያ፣ ኦይል ፖምና ብሳና ከመሳሰሉ ዛፎችና ሰብሎች የሚመረት ነው።

ባዮ ዲዝል ከተለያዩ የእፅዋት ዘይቶች የሚዘጋጅና ሙሉ በሙሉ ወይም ከናፍታ ጋር ተቀይጦ ለትራንስፖርትና የተለያዩ የናፍታ ሞተሮችን ማንቀሳቀስ ይችላል።

በተጨማሪም ለትራንስፖርት ፣ ለውሃ መሳቢያ፣ለኩራዝ መብራት፣ ለወፍጮና በገጠር አካባቢዎች ለኤሌክትሪክ ጀኔሬተር ማንቀሳቀሻም ያገለግላል።

መንግስት 2007 ዓ.ም የባዮ ፊውል ልማት ስትራቴጂ ተግባራዊ በማድረግ የባዮ ኢታኖልና ባዮ ዲዝል አቅምን ለመጠቀም ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።