የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ምክር ቤት አዳዲስ አመራሮችን ሾመ

87
ሰቆጣ ህዳር 23/2011 በአማራ ክልል የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 4ኛ ዙር 5ኛ ዓመት 3ኛ አስቸኳይ ጉባኤ የዞኑን ዋና አስተዳዳሪ ጨምሮ የሌሎች ስድስት አመራሮችን ሹመት በማፅደቅ ተጠናቀቀ። ምክር ቤቱ በጉባኤው አቶ በሪሁን ኪዳነ ማርያምን የብሄረሰብ አስተዳደር ዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አድርጎ ሾሟል ። እንዲሁም፣ አቶ ገበየሁ ወርቁን የግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ሃይሉ ጥበቡን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር መምሪያ ሃላፊ አቶ አበበ በለጠን የአካባቢ ጥበቃና የገጠር መሬት አስተዳደር መምሪያ ሃላፊ አቶ ሞገስ መርካን የጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ ሃይሌ አምሳሉን የገቢዎች ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አዱኛ ጥጋቡን የአስተዳደር ፀጥታ ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ አድርጎ በመሾም የምክር ቤቱ አስቸኳይ ጉባዔ ተጠናቋል፡፡ ዋና አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙት አቶ በሪሁን ኪዳነማርያም ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ በሰሃላ ወረዳ በመምህርነት፣ በባለሞያነትና በዋና አስተዳዳሪነት እንዲሁም በትምህርት፣ በወጣቶችና ስፖርት መምሪያዎች ላይ በሃላፊነት አገልግለዋል፡፡ አቶ በሪሁን በእቅድ ዝግጅትና አስተዳደር የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸውና በአሁኑ ወቅት በባህር ዳር ዪኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በመማር ላይ ያሉ መሆናቸውን በጉባኤው ላይ ተገልጿል፡፡ አቶ በሪሁን በወቅቱ በተለይም ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት የተጀመረውን የለውጥ ሂደት በማስቀጠል በብሄረሰብ አስተዳደር ዞኑ የሚስተዋሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችገሮች ለመፍታት የሚጠበቅባቸውን ይወጣሉ ። ምክር ቤቱ በአንድ ቀን ውሎው ከሹመቱ በተጨማሪ ያለፉት ሦስት ዓመታትን የእድገት ተኮር የእቅድ አፈፃፀምን በመገምገም አቅጣጫ አስቀምጧል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም