አካል ጉዳተኞች በስራ ትጉ በመሆናቸው ውጤታማ ናቸው-የህብረት ሽርክና ማህበር ስራ አስኪያጅ

82
አዲስ አበባ ህዳር 22/2011 'የአካል ጉዳተኞች በስራ ትጉ በመሆናቸው ውጤታማ ናቸው' ሲሉ ስድስት መስማት የተሳናቸውን ቀጥሮ የሚያሰራው ሮዛ ብርሃኑና ጓደኞቻቸው የህብረት ሽርክና ማህበር ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሮዛ ወልደአምላክ ተናገሩ። የአካል ጉዳተኞች ከስራ ቅጥር ጋር በተያያዘ የሚገጥማቸውን ችግር ለመፍታት እየሰራ እንደሚገኝ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል። አካል ጉዳተኞች በስራ ቅጥርና ምልመላ ላይ አድሎ የሚገጥማቸው ቢሆንም ሮዛ ብርሃኑና ጓደኞቻቸው የህብረት ሽርክና ማህበር ከፍ ያለ ቁጥር ያላቸውን ሰራተኞቹ መስማት የተሳናቸው አድርጓል። ይህም ውጤታማ ሊያደርገው ችሏል። በማህበሩ ተቀጥረው የሚሰሩት አካል ጉዳተኞችም ምቹ የሆነ የስራ አካባቢ እንዳላቸው ተናግረዋል። በዚህ ማህበር ውስጥ ከመቀጠሯ በፊት በሁለት የተለያየ ድርጅት ውስጥ የመስራት ዕድል ገጥሟት የነበረችው ወጣት ተዋበች ወልዴ በተማረችበት የስፌት ትምህርት የተሻለ የመፈጸም አቅም ቢኖራትም ተግባብታ ለመስራት በመቸገሯ ስራዋን ለመልቀቅ መገደዷን አስታውሳለች። ወጣት ተዋበች በሰራችባቸው ሁለት ድርጅቶች ውስጥ ከሰራተኛነት እስከ ተቆጣጣሪነት ብትደርስም መስማት የተሳናት በመሆኗ ብቻ ከመፈጸም አቅም ጋር ባልተያያዘ ችግር ስራውን መልቀቋን ገልጻለች። አሁን  ለአካል ጉዳተኞች ልዩ ትኩረት በሚሰጠው ሮዛ ብርሃኑና ጓደኞቻቸው የህብረት ሽርክና ማህበር ተቀጥራ ራስዋንና ማህበሩን እየጠቀመች ትገኛለች። በማህበሩ ተቀጥረው ከሚሰሩ ባለሙያዎች አንዷ የሆነችው ብርቅነሽ መንገሻ በበኩሏ ከዚህ በፊት ትሰራ የነበረበት ቦታ ይከፈላት የነበረው ክፍያ አነስተኛ እንደነበር ነው የነገረችን። እዚህ ከደመወዙ በተጨማሪ ስራዋን በደስታ እያከናወነች እንደሆነም ታስረዳለች። አካልጉዳተኞች የሚገጥማቸው ችግር ቢኖርም በአላማ ከሰሩ እንደማንኛውም ሰው መስራት እንደሚችሉም ገልጻለች። መስማት የተሳናቸው ሰዎች ከሌላው ኀብረተሰብ ክፍል በተሻለ መስራት እንደሚችሉ አብራ በመስራቷ እንደተገነዘበች የገለጸችው ሀናን መህዲን አሰሪዎች ለአካል ጉዳተኞች ድጋፍ በመስጠት ስራቸውን በብቃት እንዲሰሩ በማድረግ በኩል የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርባለች። የሮዛ ብርሃኑና ጓደኞቻቸው የህብረት ሽርክና ማህበር ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሮዛ ህብረተሰቡ አካል ጉዳተኞች የተሻለ የመፈጸም አቅምና የላቀ ውጤት የማምጣት ችሎታ እንዳላቸው ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም መስማት ከተሳናቸው ወገኖች ጋር ተግባብቶ ለመስራት የሚቸገር ስለሚመስለው ቀጥሮ ለማሰራት ፈቃደኛ እንደማይሆን ገልጸው፤ መስማት የተሳናቸው በስራቸው ትጉና ውጤታማ መሆናቸውን መረዳት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። ማህበሩ የሚያከናውነውን የስፌት ስራ የሚያከናውኑት ብዙዎቹ መስማት የተሳናቸው መሆናቸውን የገለጹት ወይዘሮ ሮዛ የስራው ተቆጣጣሪም መስማት የተሳናት ወጣት በመሆኗ ውጤት እያመጡ መሆኑን ተናግረዋል። አካልጉዳተኞች በቅጥር ወቅት የሚደርስባቸውን ተፅዕኖ ለመቅረፍ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን የገለፀው የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በስራ ስምሪት ረገድ የአካል ጉዳተኞች የሚገጥማቸው ፈተና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሷል። የሚኒስቴር የማህበራዊ ደህንነት ልማት ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት የግንዛቤና ትምህርት አስተባባሪ አቶ አምሃ በርሄ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አካል ጉዳተኞችም እንደሌላው ዜጋ ሁሉ የመስራት የቅጥር መብት የማግኘት ስልጠና የዝውውር እድገት የማግኘት መብት አላቸው። የስራ ማስታወቂያዎች አካልጉዳተኞችን ያካተቱ መሆን አለባቸው ያሉት አቶ አምሃ አካልጉዳተኞች በስራ ቅጥር ምልመላና መረጣ ወቅት መድሎ ከገጠመው ለሚኒስቴሩና ለሚመለከታቸው አካላት ቅሬታውን ማቅረብ እንደሚችልም ተናግረዋል። የአካልጉዳተኞች ጉዳይ የአንድ መስሪያ ቤት ብቻ ስራ ባለመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ ሁሉም የየራሱን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም