ባለፉት ዓመታት የተገኙ ድሎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የድርሻችንን እንወጣለን - የሰሜን ሸዋ ዞን አባገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች

68
ፍቼ ግንቦት 16/2010 ባለፉት ዓመታት የተገኙ ድሎችን በመጠበቅ ለአገር ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት መጠናከር የበኩላቸውን እንደሚወጡ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ አባገዳዎችና የሃገር ሽማግሌዎች አስታወቁ፡፡ ከአባ ገዳዎቹ  መካከል የአለልቱ  ወረዳ አባ ሴራ ጌታቸው ኡርጌ  በሰጡት አስተያየት ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ የኦሮሞ ህዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደርና  ቋንቋውንና ባህሉን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮለታል። የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ከመጠበቅ ባለፈ የተገኙ የሰላምና የልማት ውጤቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የአካባቢያቸውን ህብረተሰብ በማስተባበር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ አስታውቀዋል፡፡ የጅዳ ወረዳ አባ ገዳ ገለታ ደሜ  በበኩላቸው ባለፉት 27 ዓመታት ተረስቶ የቆየውና የኦሮሞ ህዝብ የዴሞክራሲ ስርዓት መገለጫ የሆነው የገዳ ስርዓት እንዲያንሰራራ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በተጨማሪም በቋንቋቸውና በባህላቸው ህዝባቸውን ለመዳኘትና ልጆቻቸውን በገዳ ስርዓት ለማነጽ እድል ማግኘታቸውንም ገልፀዋል፡፡ ''ይህን ጨምሮ የኦሮሞ ህዝብ ባለፉት ዓመታት  የተጎናፀፋቸው ሁለንተናዊ ድሎች አሳልፈን ላለመስጠት ልንጠብቀውና ልንንከባከበው ይገባል'' ብለዋል፡፡ አባ ገዳ ገለታ እንዳሉት ያላቸውን ህዝባዊ ተሰሚነት በመጠቀም ለክልሉ ሰላም መረጋገጥና ልማት መፋጠን የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል። በፍቼ ከተማ በሀገር ሽማግሌነታቸው የሚታወቁት ኮሎኔል ገዝሙ ገቢሳ በበኩላቸው ግንቦት 20 የሕዝቦች እኩልነት እንዲከበርና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲመሰረት ፅኑ መሰረት የተጣለበት ነው፡፡ በቅርቡ የተከናወነው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርም የዚህ ሥርዓት ውጤት በመሆኑ ዜጐች በመከባበርና በመተባበር ለሚያከናውኑት በጐ ተግባር ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ መክረዋል፡፡ የፍቼ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ  ሲዲሱ አበራ እንዳሉት ደግሞ አሁን የሚካሄደው የለውጥ ትግል ለራሳቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅ የድል ብስራት ነው፡፡ ከዚህ በፊት በአካባቢያቸው የተከሰቱ ግጭቶችና ሁከቶች እንዳይደገሙ ልጆቻቸውን ከመምከር  ባሻገር  በመስዋእትነት የተገኙ ሁለንተናዊ ድሎች ለፀረ ሰላም ሃይሎች አሳልፈው ላለመስጠት እንደሚታገሉም ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም