በደብረ ብርሃን ከተማ የመሰረተ ልማት ግንባታ ባለመጀመሩ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለፁ

1053

ደብረ ብርሃን ህዳር 22/2011 በደብረብርሃን ከተማ ዘንድሮ ይገነባሉ ተብሎ ለህብረተሰቡ  ቃል የተገባው የመሰረተ ልማት ግንባታ እስካሁን ባለመጀመሩ ነዋሪዎቹ ቅሬታቸውን ገለፁ።

በከተማው ዘንድሮ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታ ለማካሄድ 100 ሚሊዮን ብር መድቦ እየሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡

በደብረ ብርሃን ከተማ የቀበሌ 04 ነዋሪ የሆኑት አቶ ኢብራሂም ሁሴን እንደተናገሩት በከተማ አስተዳደሩ ይገነባሉ ተብሎ ለህብረተሰቡ ቃል የተገቡ የመሰረተ ልማት ስራ መዘግየት በእለት ከእለት እንቅስቃሴያቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እየፈጠረ ነው።

በከተማው ከብርድ ልብስ ፋብሪካ መገንጠያ አካባቢ ያለው የጠጠር መንገድ በአስፓልት ይገነባል ተብሎ በመንገዱ ዳርቻ የነበሩ ኮንቴነሮችና  የመኖሪያ ቤት አጥር ከፈረሰ ከአንድ ዓመት በላይ ቢሆነውም መንገዱ እስካሁን ባለመሰራቱ ለችግር መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ አዲስ ጥላዮ የተባሉ የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ የሚተዳደሩበት ኮንቴነር ሱቅ ለመንገድ ግንባታ ማስፋፊያ ተብሎ ከአንድ ዓመት በፊት ቢፈርሰም  ግንባታው አለመጀመሩ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ የሚሰሩ የመንገድም ሆነ የጎርፍ መፋሰሶሻ ቦዮች  ግንባታ ክረምቱ ሲገባ የሚሰሩ በመሆናቸው የጥራት ችግር እንደሚገጥማቸው የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ መሰረት መንግስቴ አመልክተዋል።

የውስጥ ለውስጥ የአስፓልትና የጌጠኛ ድንጋይ መንገዶች  አገልግሎት ሳይሰጡ መፍረሳቸውን የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዋ “በተያዘው አመት ለመገንባት ቃል የተገቡ የመሰረተ ልማት ስራዎች ባለመጀመራቸው ቅሬታ ተሰምቶኛል” ብለዋል፡፡

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ከተማ ልማት ቤቶች ኮንስትራክሽን አገልግሎት ጽህፈት ቤት የቤቶችና መሰረተ ልማት ቡድን መሪ አቶ ዳውድ ማሩ በከተማው በበጀት ዓመቱ ተለይተው ለሚከናወኑ 31 የልማት ፕሮጀክቶች 100 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡን ተናግረዋል፡፡

ከብርድ ልብስ ፋብሪካ እስከ መገንጠያ ያለው 710 ሜትር የአስፓልት መንገድን ጨምሮ 3 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የጠጠርና የጌጠኛ ድንጋይ መንገድ ንጣፍ ስራዎች እንደሚከናወኑ ቡድን መሪው አስረድተዋል፡፡

የፕሮጀክቶችን የግንባታ ስራ ለማስጀመር የዲዛይንና መሰል ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዳውድ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን የህዝቡን ቅሬታ በሚፈታ መንገድ ለማከናወን ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ለሚካሄደው የመሰረተ ልማት ግንባታ  የጥራት ደረጃውን ጠብቆ እንዲከናወን የበኩላቸውን ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉ ቡድን መሪው አሳስበዋል።

በደብረ ብርሃን ከተማ ቀደም ሲል ከ179 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት፣ የጠጠርና የድንጋይ ንጣፍ መንገድ በመስራት ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማደረግ መቻሉ ታውቋል።