በኢትዮጵያ ህገ-ወጥ የቡና ግብይት በመስፋፋት ላይ ነው ተባለ

549

አዲስ አበባ ህዳር 22/2011 በኢትዮጵያ ከቡና ንግድ ጋር በተያያዘ የሚታየው ህገ-ወጥ ግብይት መልኩን እየቀያየረ በመስፋፋት ላይ መሆኑ ተገለፀ።

ኮንትሮባንድን ጨምሮ ከቡና ንግድ ጋር በተያያዘ የሚታዩ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከል የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ድጋፍም ተጠይቋል።

ለውጭ የሚቀርብ ቡና ሳይቀር በኮንትሮባንድ መልክ ለግብይት በሚቀርብባት አዲስ አበባ ያለንግድ ፍቃድና ህጋዊ ደረሰኝ የሚፈፀመው የቡና ግብይትም እየተስፋፋ ነው ተብሏል።

የቡና ምርትን በመጋዘን አከማችቶ ለአገር ውስጥ ቸርቻሪ ማከፋፈልም እየተለመደ መምጣቱን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታውቋል። ይህም የአገሪቱን ምጣኔ ኃብት እየጎዳው መሆኑን ጠቅሷል።

የንግድ ቢሮው በየደረጃው ከሚገኙ የሴክተር አመራሮች፣ የባለድርሻ መስሪያ ቤቶችና ከንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር በዚሁ ህገ-ወጥ  የቡና ንግድ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ምክክር ዛሬ አካሂዷል።

በውይይቱ ላይ እንደተገለፀው በቡና ግብይት ላይ የሚታየው ህገ-ወጥና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በየጊዜው ስልቱን እየቀየረ በመስፋፋት አደጋ በመሆን ላይ ይገኛል ሲሉ የንግድ ቢሮው ኃላፊ አማካሪ አቶ መከታ አዳፍሬ ተናግረዋል።

ይህም የሸማቹንና ህጋዊ ነጋዴውን ጥቅም እየተፈታተነ ከመሆኑም በላይ የአገሪቱን ምጣኔ ኃብትም እየጎዳው እንደሆነ ጨምረው ገልፀዋል።

ችግሩን ለመቆጣጠርና ለመከላከል ከዚህ በፊት ከተሰሩት ጥናቶች በተጨማሪ ሌሎች አዳዲስ ጥናቶችም እየተደረጉ ይገኛሉ ያሉት አማካሪው ይህ ጥረት ስኬታማ ይሆን ዘንድ ሁሉም የሚመለከተው አካል የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይኖርበታል ብለዋል።

በቢሮው የግብርና ምርት አያያዝና አጠቃቀም ባለሙያ የሆኑት አቶ ዮሴፍ አሰፋ ከቡና ግብይት ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር አስመልክተው ባቀረቡት ገለፃ ከህገ-ወጥ ንግዱ ባሻገር ተቆጣጣሪ አካለት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዳይወጡ በህገ-ወጥ ሥራው የተሰማሩት የማደናቀፍ ተግባርም በስፋት እንዳለ ገልፀዋል።

በመሆኑም ችግሩን ማቃለል እንዲቻል የተደራጁ የቡና ነጋዴዎችን ለመከታተል፣ ለመቆጣጠር፣ ለማስተማርና ህጋዊ እርምጃ ለመወስድ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ በተለይ ህጋዊ ነጋዴው የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ ነጋዴዎች ህጋዊውን መስመር እንዲከተሉ ማድረግ፣ ቡና ተከማችቶባቸው የተዘጉ መጋዘኖችን ወደህጋዊ አሰራር  ማስገባት፣ ህጋዊ የቡና ንግድ ፍቃድ ለሸማቹና ለተቆጣጣሪዎች በሚታይ ቦታ እንዲያስቀምጡ ለማድረግ የሚያስችል ጠንካራ የቁጥጥርና ክትትል ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በተለይም የፀረ-ኮንትሮባንድ ግብረ-ሃይል ቁጥጥሩን በማጠናከር በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ የሆነ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ባለሙያው አክለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ለውጭ የሚቀርብ ቡናን ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ አገሪቱ በእጅጉ የምትፈልገውን የውጭ ምንዛሪ የሚያሳጣና አገራዊውን ምጣኔ ኃብትንም የሚጎዳ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህንን አደጋ ቡና አምራች አርሶ አደሩ ጭምር እንዲገነዘብና ከተግባሩ እንዲቆጠብ ለማድረግ የሚያስችል ግንዛቤ መፈጠር አለበት የሚል አስተያየትም ሰጥተዋል።

አቶ ካሳሁን በየነ የተባሉ ተሳታፊ አዲስ አበባ ቡና አምራች ሳትሆን ቡና ተቀባይ መሆንዋን ጠቅሰው የቡና ግብይቱ ህጋዊ ሂደቱን ተከትሎ እንዲመጣ ለአርሶ አደሩ፣ ለሹፌሮችና ለሚመለከታቸው አካላት ግንዛቤ ማስጨበጥ ተገቢ መሆኑን አሳስበዋል።

ሌላው ተሳታፊ አቶ ረመዳን ቀናው በበኩላቸው ለውጭ ገበያ መቅረብ ያለበት ቡና ለአገር ውስጥ ፍጆታ እንዳይውል ለማድረግ የሚያስችል ሰርዓት ሊዘረጋ ይገባል ብለዋል።

አቶ አማራ ቀናው የተባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ነጋዴው ህብረተሰብ የደረሰኝ ግብይት እንዲያካሂድ የግብር ትመናው ላይ ግልጽ የሆነ አሰራር መዘርጋትና ለጋዴዎች ማብራራት ያስፈልጋል የሚል ሀሳብ አቅርበዋል።

ቡና የኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብት ዋልታ መሆኑን የሚገልፁ ዘፈኖችና ማስታወቂያዎችን በማስፋፋት ዘርፉ በህዘቡ ዘንድ የሚገባውን ትኩረት እንዲያገኝ መደረግ አለበትም ተብሏል።

የቡና ምርት የውጭ ገበያ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምጣኔ ኃብት 30 በመቶ ድርሻ እንዳለው መረጃዎች ያመለክታሉ።