ለአካል ጉዳት የተዳረጉ ወገኖችን ህብረተሰቡ የመንከባከብ ኃላፊነት እንዳለበት ተገለፀ

96
መቀሌ ህዳር 22/2011 በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ሳቢያ ለአካል ጉዳት የተዳረጉ ወገኖችን ህብረተሰቡ የመንከባከብ ኃላፊነት እንዳለበት የትግራይ ክልል የአካል ጉዳተኞች ማህበር ፎረምና የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አመራሮች ገለፁ። የዘንድሮው የአካል ጉዳተኞች ቀን ''አካል ጉዳተኞችን በማብቃት አካታችነትና እኩልነታቸውን እናረጋግጥ'' በሚል መሪ ቃል ህዳር 24 ቀን በትግራይ ክልል ይከበራል። የትግራይ አካል ጉዳተኞች ማህበር ፎረም ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ ገነት ግርማይ እንደገለፁት በክልሉ እስከ 100 ሺህ የሚደርሱ አካል ጉዳተኞች ይገኛሉ። ከተጠቀሱት አካል ጉዳተኞች መካከልም የተሻለ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ያረጋገጡት ከ15 ሺህ እንደማይበልጡ ተናግረዋል። ይህም ሊሆን የቻለው ''የአካል ጉዳተኛ ጉዳይ የኔ ኃላፊነት ነው የሚል አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ ባለመኖሩ ነው'' ብለዋል፡፡ በመሆኑም ህብረተሰቡ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ሳቢያ ለአካል ጉዳተኝነት የተዳረጉ ወገኖችን የመንከባከብ ኃላፊነት እንዳለበት ተገንዝቦ የበኩሉን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ንግስቲ ወልደሩፋኤል በበኩላቸው በሃገሪቱ ለ25ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአካል ጉዳተኞችን ቀን ምክንያት በማድረግ የአካል ጉዳተኞችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት አስመልክቶ በምሁራን የፓናል ውይይት ይካሄዳል። እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም በአካል ጉዳተኝነት ዙሪያ ግንዛቤ የሚያዳብር ውይይትና የተሃድሶ ኘሮግራም በየአካባቢያቸው በማዘጋጀት ቀኑን እንደሚያከብሩ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም