በጎርጎራ ከተማ ለሚገነባው ትምህርት ቤት ከአካባቢው ተወላጆች ከ900 ሺህ ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

64
ጎንደር ህዳር 22/2011 በምእራብ ደንቢያ ወረዳ ጎርጎራ ከተማ በህዝብ ተሳትፎ ለሚገነባው የከፍተኛ ትምህርት መሰናዶ ትምህርት ቤት ከአካባቢው ተወላጆች ከ900ሺ ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ። በከተማው በ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ በህዝብ ተሳትፎ ለሚገነባው መሰናዶ ትምህርት ቤት በጎርጎራ ከተማ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ተካሄዷል፡፡ ድጋፍ ካደረጉት መካከል ወይዘሮ አስቴር አለባቸው በጎርጎራ አካባቢ በኢንቨስትመንት ስራ የተሰማሩ ባለሀብት ሲሆኑ ለሚገነባው የመሰናዶ ትምህርት ቤት 10ሺ ብር መለገሳቸውን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም ባለሀብቶችን በማስተባበር የትምህርት ቤቱ ግንባታ ተጀምሮ ለፍጻሜ እስኪበቃ ድረስ የሚጠየቁትን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የአካባቢው ሴት ተማሪዎች የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍል የመሰናዶ ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ ጎንደርና አጎራባች ከተሞች በመመላለስ የሚደርስባቸውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ያስቀራል በሚል የገንዘብ ድጋፉን ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ''ምግብ በአገልግል እያሰያዝሁ ሁለት ልጆቼ ጩሃይት ከተማ ተመላልስው እንዲማሩ አድርጌአለሁ፤ ዛሬም የአካባቢው ልጆች በዚህ ችግር ውስጥ ማለፍ የለባቸውም'' በሚል 700 ብር ለትምህርት ቤቱ ግንባታ ሰጥቻለሁ ያሉት ደግሞ አርሶአደር ግዛት መንግስቴ ናቸው፡፡ ''ወደፊትም ለትምህርት ቤቱ ማሰሪያ የሚውል የባህርዛፍ እንጨት ለማቅረብ ቃል ገብቻለሁ'' ያሉት አርሶ አደር መንግስቴ የመንግስትን እጅ ብቻ መጠበቅ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ አርሶአደር ግርማው ወንድማገኝ በበኩላቸው ''በአካባው 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ከ10ኛ ክፍል ትምህርቴን አቁዋርጬ አርሶአደር ሆኛለሁ'' ብሏል፡፡ ''10ኛ ክፍል የደረሱ ሁለት ልጆቼ የእኔ ዕጣ ፈንታ ሳይገጥማቸው በአካባቢያቸው ሆነው የትምህርት እድሉን እንዲያገኙ ለትምህርት ቤቱ ግንባታ የሚውል 600 ብር ለግሻለሁ ወደፊትም ድጋፌን አጠናክራለሁ'' ብለዋል፡፡ የጎርጎራ ከተማ ንኡስ ማዘጋጃ ቤት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንዶሰን አለም በበኩላቸው ማዘጋጃ ቤቱ ለትምህርት ቤቱ ግንባታ የ100ሺ ብር ድጋፍ ማድረጉንና የግንባታ ቦታም በነጻ መፍቀዱን ተናግረዋል፡፡ የምእራብ ደንቢያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳኜ ታደሰ በበኩላቸው የአካባቢውን ህዝብ የአርሶ አደሮችንና የባለሀብቶችን ድጋፍ ታሳቢ በማድረግ የሚገነባው የከፍተኛ ትምህርት መሰናዶ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ይጨርሳል፡፡ ''የመሰናዶ ትምህርት ቤቱ ግንባታ 10 የመማሪያ ክፍሎችን ጨምሮ ቤተ-መጻህፍትና ቤተ-ሙከራዎችን ያካተተ ነው'' ያሉት ዋና አስተዳዳሪው 600 ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ ከዚህ ቀደም ወደ ጯሂትና ጎንደር ከተማ በመመላለስ የ11ኛ የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በአስቸጋሪ ሁኔታ ይከታተሉ ለነበሩ የ11 መጋቢ ትምህርት ቤቶት ተማሪዎች ችግር የሚያቃልል ነው፡፡ መስተዳድሩ ባዘጋጀው የመጀመሪያ ዙር የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ከአርሶ አደሮች ከባለሀብቶችና ከተለያዩ አካላት 900ሺ ብር የተለገሰ ሲሆን መሰናዶ ትምህርት ቤቱም በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዟል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም