በትግራይ ክልል የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አፈፃፀም ዝቅተኛ መሆኑ ተገለፀ

87
መቀሌ ህዳር 22/2011 በትግራይ ክልል የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አፈፃፀም ዝቅተኛ መሆኑን የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ፡፡ በክልሉ ምዕራባዊ፣ ማዕከላዊና ሰሜን ምዕራብ ዞኖች በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች በተካሄደው ዳሰሳ አፈጻጸሙ በሚፈለገው መንገድ እንዳልሆነ ተገልጿል፡፡ በፍትህ ቢሮ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ዳይሬክተር አቶ ገብረሃዋሪያ ወልዱ እንዳሉት የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ካለፉት ጊዜያት አንፃር መሻሻል ቢያሳይም ውጤቱ ግን የሚፈለገው ያህል አይደለም፡፡ ለአፈጻጸሙ መዳከም ስራውን እንዲመሩት በየደረጃው የሚገኙ አካላት ለስራው ትኩረት ባለመስጠታቸው ነው፡፡ በቢሮ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ተተኪ ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ሃዋዝ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት 91 ሺህ 859 የልደት፣ ሰርግ፣ ፍቺና ሞት ምዝገባ ለማካሄድ ታቅዶ 74 ሺህ 729 የነባር ኩነት ምዝገባ መካሄዱን ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥም ምዝገባ ለማካሄድ ከታቀደው ከ23 ሺህ በላይ ኩነት ውስጥ የተከናወነው 18 ሺህ 699 ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የፀገዴ ወረዳ ፍትህ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለም ኪሮስ እንዳሉት ምዝገባው ከ2008 ዓ.ም የተጀመረ ቢሆንም ባለድርሻ አካላት ለስራው የሰጡት ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ የተመዝጋቢው ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የወረዳና የቀበሌ አስተዳደሮች ወሳኝ ኩነት ምዝገባን ተደራቢ  ስራ አድርገው መውሰዳቸው ለአፈፃፀሙ መዳከም ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም የወሳኝ ኹነት ምዝገባን ጥቅም በውል ባለመገንዘባቸው ለአፈጻጸሙ መዳከም ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እንደስራ አድርጎ ያለማየት ዝንባሌና አስተሳሰብ ስላለ ወደ ኋላ ቀርተናል ያሉት ደግሞ በወልቃይት ወረዳ ፍትህ ፅህፈት ቤት ተጠሪ አቶ ካሳዬ ዘፈሩ ናቸው። የዓዲ ረመፅ ከተማ ወሳኝ ኩነት ፅህፈት ቤት ተጠሪ ኪዳነማርያም ገብረዮሃን በበኩላቸው  የህብረተሰቡ ግንዛቤ ዝቅተኛ በመሆኑ የወሳኝ ኩነት ተመዝጋቢው ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሓጎስ ጎድፋይ ''የልደት ምዝገባ በዋናነት ጤና ቢሮ ስለሚመለከተው  በየደረጃው ያሉትን ጤና ተቋማት በመፈተሽ በምዝገባ የታዩት ድክመቶች ለማረም ዝግጁ ነን'' ብለዋል፡፡ በየሶስት ወሩ ስራውን በመፈተሽም ሰራው በአግባቡ በማይሰሩ ባለሙያዎች ላይ እርምጃ  እንደሚወሰድ ገልፀዋል፡፡ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ንግስቲ ወልደሩፋኤል በበኩላቸው ''ወሳኝ ኩነት ምዝገባ የህብረተሰቡ መብት በመሆኑ ይኸው እንዲከበር በተለየ ትኩረት እንሰራለን'' ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም