ለጋምቤላ ክልል የልማት ጥያቄ መመለስ የወጣቱ ተሳትፎ ወሳኝ ነው---የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር

119
ጋምቤላ ህዳር 22/2011 የጋምቤላ ክልልን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የወጣቱ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ-መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስታወቁ። ርዕሰ-መስተዳድሩ ከጋምቤላ ከተማ ወጣቶች ጋር በሰላምና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሄደዋል። በውይይቱ ወቅት አቶ ኡሞድ እንደተናገሩት ወጣቱ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ በተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ላይ ተሳትፎውን ሊያጠናክር ይገባል። በተለይም ወጣቱን በማሳሳት የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ የሚሞክሩ ኃይሎችን ተንኮል በማጋለጥ ረገድ የወጣቶች ኃላፊነት ከፍተኛ እንደሆነም ተናግረዋል። ባለፉት ዓመታት ተንሰራፍቶ የነበረው የተደራጀ ሌብነት፣ ሙስናና የብልሹ አስራር ችግሮች የክልሉን ልማት ብቻ ሳይሆን የወጣቱን የልማት ተጠቃሚነት ጭምር ጎድቶት መቆየቱን ተናግረዋል። በተለይም በከተማ መሬትና ለህዝብ በሚቀርቡ የመሰረታዊ ሸቀጦች ስርጭት ላይ አመራሩ ህዝብን ሳይሆን እራሱንና ቤተሰቡን ሲያስጠቅም መቆየቱን ገልጸዋል። እነዚህን የተበላሹ የአስራሮች በማስቆም የህዝቡን በተለይም የወጣቱን ተጠቀሚነት ለማረጋገጥ የክልሉ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ኡሞድ ኡቻላ በሰጠው አስተያየት አዲሱ አመራር ጠንክሮ መምራት ከቻለ ወጣቱ ከጎናቸው በመሰለፍ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል። ሌላው ተሳታፊ ወጣት ጋትዊች ቢድድ በበኩሉ የአመራር ለውጡ በዕርሳነ-መስተዳድሮች ብቻ ሳይሆን በሌሎች አመራሮች ላይም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ከአሁን በፊት በነበሩት አመራሮች በአፍ ብቻ እየተደለሉ ወጣቱ የልማቱ ተጠቃሚ ሳይሆኑ መቆየታቸውን የገለጸው ደግሞ ወጣት አንድነት አረጋ ነው። በመሆኑን ከአሁን በኋላ የቃላት ሽንገላን ሳይሆን ሰረተው እራሳቸውና አካባቢያቸውን የሚለውጡበት ስራ እንዲመቻቸላቸው ጠይቋል። ርዕሰ መስተዳደሩን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የውይይት መድረክ ላይ ከ350 የማያንሱ ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም