የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጭ ግንባር አመራሮች አዲስ አበባ ገቡ

86
አዲስ አበባ  ህዳር 22/2011 የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) ከፍተኛ አመራሮች በሠላማዊ መንገድ ፖለቲካዊ መርኃ ግብሩን ለማራመድ ዛሬ አዲስ አበባ ገቡ። አመራሮቹ አዲስ አበባ ሲደርሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች  አቀባበል አድርገውላቸዋል። የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጭ ግንባር ዋና ጸኃፊ አብዱልረህማን መህዲ ፓርቲያቸው ከበርካታ ዓመታት በኋላ ወደ አገራቸው መመለስ መቻሉ  እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል። ይህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ መሆኑን ገልጸው፤ ፓርቲያቸው በአገሪቱ ያለውን ለውጥ በአዎንታዊ እንደሚመለከተው አስረድተዋል። ''ይህም ለሶማሌ ህዝብ ትልቅ አበርክቶ አለው'' ያሉት ዋና ጸኃፊው አሁንም ከፌዴራል መንግሥት ጋር አብሮ በመሥራት የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ሙስጠፋ ኡመር በበኩላቸው ፓርቲው ወደ አገር ቤት መመለሱ ለሶማሌ ህዝብና ለሶማሌ ክልል ትልቅ ፖለቲካዊ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል። ይህም ለሶማሌ ህዝብ ሠላም ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ገልጸው፤ ከዚህ በኋላ ከፓርቲው ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ክልሉ ሠላሙን አረጋግጦ ልማት ላይ እንዲያተኩር የሚያግዘው መሆኑን አመልክተዋል። የገንዘብ ሚኒስትርና የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር አቶ አህመድ ሺዴም በተመሳሳይ ኦብነግ ወደ አገር ቤት መምጣቱ ለክልሉ ህዝብ ሰላምና መረጋጋት ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል። ከዛም ባለፈ የክልሉ ህዝብ አንድነቱ እንዲጠናከርና በጋራ በመሆንም ልማት ላይ ትኩረት ለማድረግ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል። መቀመጫውን በኤርትራ አድርጎ የነበረው ኦብነግ ከተቋቋመ 24 ዓመታት ሆኖታል። በዛሬ ዕለትም የግንባሩን ሊቀመንበር  አድሚን ሞሃመድ ኦማር ኦስማንና ዋና ጸኃፊ አብዱልርሃማን መህዲን ጨምሮ ሌሎች 25 የፓርቲው አመራሮችን ይዞ አዲስ አበባ ገብቷል። በሌሎች የዓለም አገሮች ያሉት የተቀሩት የግንባሩ አባላቶች ደግሞ ከዚህ በኋላ ወደአገር ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቅሷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም