የአነስተኛ ፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት አሰራራቸውን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ማድረግ እንደሚገባቸው ተገለፀ

72
መቀሌ ህዳር 22/2011 የአነስተኛ ፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት ለህብረተሰቡ የሚሰጡት አገልግሎት ቀልጣፋና ተወዳዳሪ እንዲሆን አሰራራቸው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ማድረግ እንደሚገባቸው ተገለፀ፡፡ በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ለአራት ቀናት ሲካሄድ የቆየው አገር አቀፍ የአነስተኛ ፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት አመታዊ የምክክር መድረክ ትላንት ማምሻውን ተጠናቋል፡፡ የኢትዮጵያ አነስተኛ የፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት ማህበር ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ከበደ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በአገሪቱ ያሉት የአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ወደ ህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድግና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት አሰራራቸውን መፈተሽ ይገባቸዋል፡፡ አገልግሎት አሰጣጣቸውን ቀልጣፋ ለማድረግም በኮምፒተር የታገዘ የኮር ባንኪንግ አገልግሎት ወደሚሰጡበት ደረጃ መሸጋገር እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ 5 ሚሊዮን የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ  ደንበኛ ያለቸው 38 አነስተኛ የገንዘብ አበዳሪ ተቋማት እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ''ተቋማቱ እስከ አሁን 50 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ በማበደር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኝ ማህበረሰብ ተደራሽ እየሆኑ ናቸው'' ብለዋል፡፡ የማይክሮ ፋይናንሶቹ የቁጠባ አቅምም ወደ 30 ቢሊዮን ብር ከፍ ማለቱን አቶ ተሾመ ገልጸዋል፡፡ ተቋማቱ አሁን የደረሱበት ደረጃ ይበልጥ ተደራሽና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አሰራራቸው ማዘመን እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡ ከትግራይ አደዳይ ማይክሮ ፋይናንስ የተወከሉ አቶ ክብረአብ ኣሳየኸኝ በበኩላቸው መድረኩ ህብረተሰቡን በይበልጥ ለማገልገል እስከአሁን የሄዱበትን አሰራር የዳስሱበት እንደነበር ገልጠዋል። አገልግሎቱን ፈጣን ለማድረግም ስራቸው በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን ማድረግ ማስፈለጉን በምክክር መድረኩ ትኩረት ካገኙ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከሸገር ማይክሮ ፋይናንስ የተወከሉት  አቶ ካሳዬ አየለ እንደገለጹት  የምክክር መድረኩ ህብረተሰቡን በይበልጥ ለማገልገል በመካከላቸው ያለው መልካም ተሞክሮ የቀሰሙበት መሆኑን ገልጠዋል። በምክክር መድረኩ በብድርና ቁጠባ ተቋማት ዙሪያ ያተኮሩ ጥናቶች የቀረቡበትና ለቀጣይ እንዴት መስራት እንዳለባቸው የተገነዘቡበት መድረክ መሆኑን የገለፁት ደግሞ ከአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም የመጡት አቶ ተዋበ አይሸሽም ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም