በቤተ እምነትና ሃይማኖታዊ በዓላት ላይ የሚታዩት የመከባበርና የመቻቻል እሴቶች መስፋትእንዳለባቸው ተጠየቀ

62
አክሱም ህዳር 22/2011 የሀገር ፍቅር፣ አንድነትና ሰላምን ለማስቀጠል በቤተ እምነትና ሃይማኖታዊ በበዓላት ላይ የሚታዩት የመከባበርና የመቻቻል እሴቶች መስፋት እንዳለባቸው ተጠየቀ፡፡ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ወደ አክሱም የመጡ የበዓሉ ታዳሚዎች በትላንትናው ዕለት በዓሉን በጋራ አክብረዋል፡፡ በየአከባቢው በተደረገላቸው አቀባበል መደሰታቸውን የተናገሩት የበዓሉ ተሳታፊዎች በቤተ እምነትና ሃይማኖታዊ በበዓላት ላይ የሚታዩ የመቻቻልና የመከባበር እሴቶቹን በሁሉም ቦታዎች በማስፋት የዕለት ተዕለት ተግባር ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ከኦሮሚያ ክልል ዝዋይ ከተማ የመጡት  ወይዘሮ አልጋነሽ ግርማዬ ለኢዜአ እንደገለጹት በህዳር ጸዮን ሃይማኖታዊ በዓል ላይ በህብረተሰቡ መካከል የታየው  የኢትዮጵያን ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት በሁሉም ቦታዎች ሊታይ ይገባል። በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት የህዝቡን አንድነት በማጠናከር ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው የገለጹት የበዓሉ ተሳታፊ እያንዳንዱ ዜጋ መልካም እሴቶች እንዲጠናከሩ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ  ተናግረዋል፡፡ "ኢትዮጰያዊ  ሰው አክባሪና እንግዳ ተቀባይ ነው" ያሉት ወይዘሮ አልጋነሽ ህዝቡ  በሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ላይ የሚያሳየውን የመከባበርና መቻቻል እሴት በሁሉም ቦታዎች በማሳየት ለሀገር አንድነትና ሰላም መጠናከር ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ በሃይማኖታዊና ባህላዊ  በዓላት ላይ የሚታዩት የመፈቃቀርና የመቻቻል እሴቶችን ተጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል ያሉት ደግሞ በበዓሉ ለመሳተፍ ከቤተሰባቸው ጋር ከአዲስ አበባ ከተማ የመጡት አቶ ተስፋዬ በርሄ ናቸው። ከአዲስ አበባ ሲመጡ ከመግቢያ ኬላዎች ጀምሮ የአከባቢው ህዝብ በየቦታው ምግብ በመያዝ ደማቅ አቀባበል እንዳደረገላቸው አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል። የኢትዮጵያውያን ባህላዊ መገለጫዎች የሆኑትን እነዚህ መልካም እሴቶች ማስቀጠል እንደሚገባ አቶ ተስፋዬ አሳስበዋል። ለኢትዮጵያውያን  የሚበጀው ብሔር በመቁጠር ግጭት መፍጠርና መራራቅ ሳይሆን ተባብሮና  ተቻችሎ አንድነታችንን በማስጠበቅ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ከመቀሌ  ከተማ የመጡት ወይዘሮ መብራት መረሳ በበኩላቸው በህዳር ፅዮን በዓል ላይ የኢትዮጵያውያንን የፍቅር፣ ሰላም እና የአንድነት  ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ "ከተለያዩ አከባቢዎች ከመጡ ኢትዮጵያውያን ጋር ያለንን ተካፍለን፣ አንድ ላይ ሰለአንድነታችን ስለ ሀገራችን ሰላም መጠበቅ እየተጫወትን በዓሉን አክብረናል" ሲሉ ወይዘሮ መብራት አመልክተዋል፡፡ በእንደዚህ አይነት ሃይማኖታዊ በዓላት ላይ የሚታየውን ፍቅር፣ ሰላም እና አንድነት በማስቀጠል  እርስ በእርስ ተከባብሮና ተቻችሎ መኖር እንደሚገባ መብራት ጠይቀዋል። በበዓሉ የተገኙት መልአከ ጸሐይ መምህር መልአኩ ሙላው በበኩላቸው "ሁሌም እሳቤያችን ስለ ሰላም መሆን አለበት ሰላም ለማንም የሚሰጥ አይደለም በራስ ነው የሚጠበቀው" ብለዋል። የሃይማኖት መሪዎች ስለ አገር አንድነትና ስለ ሰላም ምዕመናንን ማስተማር እንደሚገባቸው የተናገሩት መምህር መላኩ ሰላምን ለማሰጠበቅ የሃይማኖት ተቋማት ትልቅ ሚና መጫወት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም