የብሄር ብሄረሰቦች በዓል በየክልሉ የምጣኔ ኃብት መነቃቃት እንዲፈጠር መልካም አጋጣሚ ሆኗል

69
አዲስ አበባ ህዳር 22/2011  የብሄር ብሄረሰቦች በዓል በየክልሉ መከበሩ በህዝቦች መካከል መቀራረብንና መተዋወቅን ከመፍጠር ባሻገር በተለይ በታዳጊ ክልሎች የምጣኔ ኃብት መነቃቃት እንዲመጣ እያደረገ መሆኑን የፌደሬሽን ምክር ቤት ገለፀ። የኢፌዴሪ ህገ-መንግሥት የፀደቀበት ህዳር 29 ቀን የብሔር ብሔረሰቦች ክብረ በዓል እንዲሆን በፌዴሬሽን ምክር ቤት ከተወሰነ ዘንድሮ 13ኛ ዓመቱ ላይ ይገኛል። ቀኑ የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን አንድነት ለማጠናከር፣ የእርስ በርስ ትውውቅ መድረክ ለመፍጠርና የህዝቦችን ባህልና ወግ ለማሳደግ በሚል መሰረታዊ ዓላማ ነው። በዚህም መሰረት ቀኑ ላለፉት 12 ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በተራ እየተከበረ ይገኛል። ክብረ-በዓሉ የብሄርና ብሄረሰቦች መብትን ከማስከበር ባሻገር ባህላቸውን ጨምሮ አጠቃላይ ማንነታቸው እንዲታወቅ፣ አስፈላጊው ጥበቃና ክብካቤም እንዲደረግለት መልካም አጋጣሚ እየፈጠረ ያለ ክዋኔ እንደሆነ ይነገራል። በዓሉ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በዙር እንዲከበር መደረጉ ደግሞ ምጣኔ ኃብታዊ ፋይዳንም እያመጣ መሆኑን ነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚገልፀው። ወይዘሪት ፍሬዌይኒ ገብረእግዚአብሄር በፌዴሬሽን ምክር ቤት የዲሞክራሲያዊ አንድነት፣ የሕገ-መንግሥት አስተምህሮትና የሠላም ግንባታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጸሀፊ ሲሆኑ የዘንድሮው ብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓል ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴም ጸሀፊ ናቸው። እንደ እርሳቸው ገለጻ የብሄር ብሄረሰቦች በዓል የብሄሮችን ትስስር ከማጎልበት ባሻገር የምጣኔ ኃብት መነቃቃት እንዲፈጠር አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። በዓሉ በሚከበርበት ክልል አዳዲስ ሆቴሎች ግንባታ፣ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲሁም የሥራ ዕድል ፈጠራዎች እንዲያብቡ ማገዙን ይናገራሉ። በዓሉ በተለይ አገልግሎት ዘርፉ ላይ አዳዲስ ሆቴሎች እንዲገነቡ ማስቻሉን የጠቀሱት ወይዘሪት ፍሬዌይኒ ኢንቨስተሮችም ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመሄድ መዋእለንዋያቸውን እንዲያፈሱና ዜጎችም የሥራ አድል እንዲያገኙ  ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አብራርተዋል። በዓሉ የተከበረባቸው ክልሎች ከበዓሉ በፊትና ከበዓሉ በኋላ ያሉበት ተጨባጭ ሁኔታ ሲነጻጸር መሰረታዊ ለውጥ ማሳየታቸውንም ጠቀሰዋል። ለአብነትም ባለፈው ዓመት የብሄር ብሄረሰቦች በዓል በአፋር ክልል መከበሩን አስታውሰው በዓሉን ተከትሎ የ36 ሆቴሎች ግንባታ መጀመሩን አስረድተዋል። ጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾች የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩም ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል። አዲስ አበባ ዘንድሮ ለአሥራ ሦስተኛ ጊዜ የሚከበረውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ታስተናግዳለች። በመጪው ሳምንት የሚከበረው በዓሉ “በብዝሃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊነት ለአንድነት” በሚል መሪ ቃል ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም