የፖለቲካ አመራሩ ለሰላም እሴት ግንባታና ለህዝቦች አብሮነት ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲሰራ ተጠየቀ

120
ሰመራ ህዳር 22/2011 የፖለቲካ አመራሩ ለሰላም እሴት ግንባታና ለህዝቦች አብሮነት ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲሰራ ሴት የሰላም አምባሳደሮች ጠየቁ፡፡ ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡት ሴት የሰላም አምባሳደሮች ከአፋር ክልል ምክትል አፈ-ጉባኤ ጋር ትላንት ተወያይተዋል፡፡ በህዝቦች ሰላምና አብሮነት ላይ ያተኮረ ውይይት ከአፋር ክልል ምክትል አፈ-ጉባኤ ጋር  ያደረጉት ሴት የሰላም አምባሳደሮች የፖለቲካ አመራሩ ለሰላም እሴት ግንባታና ለህዝቦች አብሮነት ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡ ከኦሮሚያ ክልል የመጡት ወይዘሮ አዱኛ አህመድ በውይይቱ ወቅት አንደተናገሩት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያለምንም የእምነትና አመለካከት ልዩነት ለዘመናት አብረው በመኖር  መልካም አሴቶቻቸውን ለትውልድ አስረክበዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ አገሪቱ አካባቢዎች በህዝቦች መካከል የነበረውን አብሮነት የሚሸረሽሩ ድርጊቶች መፈጸማቸው እንዳሳዘናቸው ወይዘሮ አዱኛ ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ድርጊቶች ለግጭቶች ምክንያት መሆናቸውን ያመለከቱት የሰላም አምባሳደሯ የዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራት ሁኔታ አደጋ ውስጥ እየወደቀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ፖለቲከኞችም ሆነ  የሀገሪቷ ሰላምና የህዝቦች አብሮነት ያሳስበናል የሚል ኢትዮጵያዊ  የሚያስተላልፏቸውን መልዕክቶች ለህዝቦች አብሮነትና ለሰላም ያለውን ፋይዳ መዝነው ሊሆን እንሚገባ ወይዘሮዋ አመልክተዋል፡፡ ከሀረሪ ክልል የመጡት ወይዘሮ ገነት አሰፋ  የአፋር  ህዝብ በማንነቱም ሆነ በእምነቱ ሳይሳቀቅ በነጻነት አብሮ ተከባብሮና ተቻችሎ በመኖር ለሌሎች የሀገሪቱ ክልሎች ተምሳሌት የሚሆን መሆኑን ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህ የሰላም እሴት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በሃላፊነትና በትጋት እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡ ከሱማሌ ክልል የመጡት ወይዘሮ አብሽሩ መሐመድ በበኩላቸው "ቤተሰቦቻችን በሰላም ወጥተው መግባት የሚችሉት ሰላም ሲረጋገጥ ብቻ ነው" ብለዋል፡፡ "ሰላም ከቤተሰብ የሚጀመር ነው" በማለት ያስረዱት ወይዘሮ አብሽሩ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ፖለቲከኛውን ጨምሮ ከቤተሰቡና ከጎረቤቱ ጋር ያለው ግንኙነት ሰላምንና ፍቅር፤ መከባበርና መቻቻልን መሰረት ያደረገ ከሆነ ልጆቹም  ሰላም ወዳድና ሰው አክባሪ መሆን እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ የአፋር ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አሚና ሴኮ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት  ከሴት የሰላም አምባሰደሮች የተሰጣቸውን ምክረ ሃሳብ እስከታችኛው የአስተደደር እርከን እንዲወርድ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡ ሰላም ከምንም ነገር በፊት ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲሰራ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የገለጹት ምክትል አፈ-ጉባኤዋ የሴት አምባሳደሮች ተግባር መንግስት የሀገር በቀል የግጭት አፈታትና የሰላም እሴት ግንባታ ላይ እሴቶችን በመጠቀም ችግሮችን ለመፍታት የጀመረው ጥረት ማሳያ መሆኑን አመልክተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም