የመሰረተ ልማት እጦት የዕለት ህይወታችን ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል...የትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ነዋሪዎች

59
ሽሬ ህዳር 21/2011 የውሃ የመንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት ችግሮች የዕለት ህይወታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን የትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ። በጥናት ላይ የተመሰረቱ ስራዎችን በማከናወን ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ መንግስት አስታውቋል። ከዞኑ ከላእላይ አዲያቦ ወረዳ የመጡ የውይይቱ ተሳታፊ መልአከ ሰላም ናርዶስ ገብረስላሴ በሰጡት አስተያየት በዞኑ ያሉት ስር የሰደዱ የመሰረተ ልማት ችግሮች ነዋሪውን ለእንግልት እየዳረጉት ነው። ለንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ለመንገድ ችግሮች ትኩረት ተሰጥቶ መፍትሔ እንዲገኝላቸው ከምክትል ርዕሰ-መስተዳደሩ ጋር ያደረጉት ውይይት ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል። “በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረው ሰላምና ፍቅር ስር እንዲሰድ የክልሉ መንግስት እያደረገው ያለው ጥረት የላቀ ነው” ያሉት ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ድንቅነሽ ታፈረ ናቸው። በመንገድና በሌሎችም አማራጮች ግንኙነቱን ለማሳደግ የመሰረተ ልማቱ መሟላት እንዳለበት አመልክተው ሰላምና ልማትን ለማደናቀፍ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ መቆም እንዳለበትም ተናግረዋል። ከዞኑ ፀለምት ወረዳ የመጡት አቶ አዲሴ በላይ በበኩላቸው እንዳሉት በመልካም አስተዳድር ዙሪያ የሚስተዋሉትን ችግሮች ለመፍታት የክልሉ መንግስት ትኩረት ማድረግ ይኖርበታል። የአካባቢው ሰላም በዘላቂነት እንደተጠበቀ እንዲቆይም የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል። በውይይቱ ላይ ምክትል ርዕሰ-መስተዳደሩ እንደተናገሩት በአካባቢያቸው በቂ የውሃ፣ የመንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮችን ለማሟላት የክልሉ መንግስት ጥረት እያደረገ ይገኛል። ከንጹሕ የመጠጥ ውሀ አቅርቦት ተያይዞ የተነሳው ችግር በዞኑ ብቻ ሳይሆን በክልል ደረጃ እያጋጠመ ያለ ችግር መሆኑንም ገልጸዋል። ይሔን በዘላቂነት ለመፍታትም በክልሉ ያለውን የመጠጥ ውኃ አቅርቦትና እጥረት በአዲስ መልክ የሚያጠና አንድ የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “ቡድኑ በሚያቀርበው ጥናት መሰረት እንደ ችግሩ ስፋትና ጥልቀት እየታየ ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ጥረት ይደረጋል" ብለዋል። “ከገጠር መንገድ ጋር በተያያዘ ለተነሳላቸው ጥያቄም ሁሉንም ችግሮች በአንድ ጊዜ ለመፍታት ቢያስቸግርም ቅድሚያ ትኩረት የሚያስፈልጋቸውን በመለየት የመንገድ ግንባታው እየተካሄደ ነው” ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የምትገናኝባቸውን መንገዶች ክፍት በማድረግ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር በፌዴራል መንግስትና በክልሉ  ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ "ከኤርትራ ጋር የተጀመረውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የተጀመረው ሰላም ስር እንዲሰድ ማድረግ አለብን" ብለዋል። በውይይቱ የተገኙት የተለያዩ ቢሮ ኃላፊዎች በውይይቱ ተሳታፊዎች የተነሱት የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እንዲፈቱ የራሳቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ገልፀዋል። በውይይቱ ከሃይማኖት መሪዎች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከንግዱ ህብረተሰብና ከሲቪክ ማህበራት የተውጣጡ ከአንድ መቶ አምሳ በላይ ሰዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም