የአሜሪካ መጤ ተምችን ለመከላከል የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጀ

70
አዲስ አበባ ግንቦት 16/2010 የአሜሪካ መጤ ተምች በግብርና ምርት ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ለመከላከል የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ መዘጋጀቱን የግብርናና እንስሳት ሃብት ሚኒስቴር ገለጸ። ስትራቴጂክ እቅዱ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን አምስት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ እንደሆነ ተገልጿል። የአሜሪካ መጤ ተምች አሁን ያለበትን ሁኔታና የ2010/11 ዓ.ም የምርት ዘመን ቅድመ ዝግጅትን በተመለከተ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል። በሚኒስቴሩ የዕፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዮስ ሰላቶ እንዳሉት፤ ባለፈው ዓመት በድንገት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ባሉ ሰብሎች ላይ በመከሰት ጉዳት አድርሷል። በዚህም የጉዳት መጠኑ እንደየአካባቢዎቹ የተለያየ ቢሆንም ችግሩ በተከሰተባቸው ሰብሎች በአማካኝ የአምስት በመቶ ጉዳት እንዳደረሰ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ዘንድሮ አብሮ የከረመ ከመሆኑና ከጎረቤት አገሮች በቀላሉ መግባት ስለሚችል በጥንቃቄ መከላከል ስለሚገባ ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቷል ብለዋል። በዚህም ቅንጅታዊ አሰራር፣ ግንዛቤ ፈጠራ፣ ቅኝት ዳሰሳና ትንበያ፣ በባህላዊና ዘመናዊ መንገድ የተቀናጀ የመከላከል ስርዓት እንዲሁም የምርምር ስራዎችን አካቶ ስትራተጂክ ዕቅዱ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል። የአሜሪካን መጤ ተምች ለመከላከል በአርሶ አደሮች፣ በወረዳ፣ በዞን፣ በክልልና በአገር ደረጃ ተቀናጅተው መስራት ካልቻሉ ሰብሎችን ከጥቃት ማዳን እንደማይቻል አስገንዝበዋል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የአፍሪካ አገሮች በቅንጅት መስራት ብቸኛ አማራጫቸው እንደሆነ ማስቀመጡ አይዘነጋም። በኢትዮጵያ ያለው የአሜሪካ መጤ ተምች በአግባቡ ቁጥጥር ካልተደረገበት 73 በመቶ ሰብል ሊያጠፋ እንደሚችል ትንበያ መኖሩን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ካለፈው ዓመት በተሻለ መንገድ ቅድመ ዝግጅት ከተደረገ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ይቻላል ብለዋል። የአሜሪካ መጤ ተምች በአፍሪካ በኮንጎ 80 በመቶ፣ እንዲሁም በዚምባብዌ 75 በመቶ ያህል ጉዳት አድርሶ እንደነበር ገልጸዋል። በኢትዮጵያ በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ጋሞ ጎፋ ዞን ተምቹ በተከሰተባቸው 13 ወረዳዎች 35 በመቶ፣ ጋምቤላ 17 በመቶ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን በአገሪቱ በአማካኝ ያደረሰው ጉዳት አምስት በመቶ መሆኑን ጠቁመዋል። ከ100 በላይ ሰፋፊ ቅጠል ያላቸውን አዝዕርት የሚያጠቃው ይኸው ተምች መሬት ውስጥ ተደብቆ ስለሚቆይ አርሶ አደሮች መሬቱን ደጋግሞ በማረስ በጸሀይ ሃይል እንዲሞት ማድረግ የሚችሉበት አማራጭ መኖሩን ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ እርጥበት በሚበዛባቸው ቦታዎች፣ እንዲሁም በአረም ላይ ተደብቆ ስለሚቆይ መሬታቸውን ከአረም ማጽዳትና ደጋግሞ ማረስ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። በዚህ ዓመት ኅብረተሰቡና አመራሩ ችግሩን ለመከላከል የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ እንደሚታይበት የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ ችግሩ ከአምናው የባሰ ሊሆን ስለሚችል መዘናጋት አይገባም ብለዋል። አርሶ አደሩ ጸረ ተባይ መድሃኒት መጠቀም ያለበት የመሬቱ 10 በመቶ በተምች ከተወረረና የመጨረሻ አማራጭ ሲያጣ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ቢሮ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ብርሃኑ በበኩላቸው፤ በዚህ ዓመት በኦሮሚያ፣ አማራ፣ አፋር፣ ትግራይ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብና ሶማሌ ክልሎች ተከስቶ እንደነበር ገልጸዋል። በዚህም በአጠቃላይ በመስኖ የለማውን 353 ሺህ 201 ሄክታር መሬት የወረረ ሲሆን 29 ሺህ 926 ሄክታር መሬት መከላከል መቻሉን አስረድተዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም