የከፍተኛ ትምህርት የጥናትና ምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክር ቤት ሊቋቋም ነው

100
አዲስ አበባ ህዳር 21/2011 የከፍተኛ ትምህርት የጥናትና ምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክር ቤት ሊቋቋም መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ። የምክር ቤቱ መቋቋም የጥናትና ምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስርን ለማጠናከርና የማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት ያለመ እንደሆነ ተጠቁሟል። በምክር ቤቱ  አመሰራረት ዙሪያ በተደረገው ውይይት የሁሉም የመንግስትና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምክትል ፕሬዚዳንቶች ተሳትፈዋል። ምክር ቤቱ በአንድ ወር ውስጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከተወያዩበት በኋላ ወደ ተግባር እንደሚገባና የካውንስሉ ሊቀመንበርም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ እንደሚሆኑ ተገልጿል። የዩኒቨርሲቲ የጥናት፣ ምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ የግል ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኢንስቲትዩት፣ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኤጀንሲ የምክር ቤቱ አባላት ሲሆኑ የከፍተኛ ትምህርት የጥናትና ምርምር ጉዳዮች ዳሬክቶሬት የካውንስሉ ፀሀፊ ይሆናል ተብሏል። የምክር ቤቱ መቋቋም የጥናትና ምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ግንኙነት ለማጠናከር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል እንደሚሆን ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ተናግረዋል። የተለያዩ ጥናቶች በዩኒቨርሲቲዎች ሲካሄዱ እርስበስር ልምድ ለመለዋወጥና ቴክኖሎጂን ለማላመድ እንደሚያግዝ ገልጸዋል። ምክር ቤቱ በየሩብ ዓመቱ በመገናኘት የተገኙ ውጤቶች፣ ያጋጠሙ ችግሮችን በመለየት አቅጣጫ ያስቀምጣል ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲዎች ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር 70 በመቶ በመማር ማስተማሩ እና 30 በመቶ በጥናትና ምርምር የነበረውን አሁን 60 በመቶ በመማር ማስተማሩ ላይ፣ 25 በመቶ በጥናትና ምርምር እና 15 በመቶ በማህበረሰብ አገልግሎት ወይም በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ እንዲሆን ተደርጓል። በውይይቱ የተነሳው ሌላው ጉዳይ ዩኒቨርሲቲዎች የተሟላ ላቦራቶሪ እንዲያሟሉ የሚያስችል መመሪያ ማዘጋጀትን የተመለከተ ሲሆን በኤሌክትሪካልና ሲቪል ምህንድስና፣ ባዮሎጂ፣ ፊዚክስና ኬሚስትሪ በመጀመሪያ ዲግሪ ዩኒቨርሲቲዎች የተሟላ ላቦራቶሪ እንዲኖራቸው የሚያስገድድ እንዲሆን የሚደረግ መሆኑ ተጠቁሟል። በኢትዮጵያ የመጀመሪያ በሆነው የጥናትና ምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር እና የማህበረሰብ አገልግሎት መመሪያ ላይ ውይይት ተደርጓል። የሚሰሩት ጥናት ምርምሮች በአገሪቱ ፖሊሲ አቅጣጫ መሰረት መሆን እንዳለባቸውና ምርምሮቹ የኀብረተሰቡን፣ የአገሪቱን ችግር ፈቺ በሆነ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ እንዲሆኑ ትኩረት ይደረጋል። በውይይቱ ላይ የተገኙ የዩቨርሲቲ አመራሮች በበኩላቸው የአዋጁ መዘጋጀት ከዚህ በፊት በላቦራቶሪ ረገድ የሚታየውን ችግር በመቅረፍ ይወጣ የነበረውን ተጨማሪ ወጪ እንደሚያስቀር ገልጸዋል። ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ከደብረብረሃን ዩኒቨርሲቲ የመጡት ዶክተር አልማዝ አበራ እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊት ላቦራቶሪን ለመጠቀም ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ሲሄድ በአንድ ጊዜ ብቻ 250 ሺህ ብር ወጪ ያደርጋል። የመመሪያው መጽደቅ ይህንን መሰል ችግር እንደሚፈታ ገልጸዋል። መመሪያ ባለመዘጋጀቱ ለጥናትና ምርምር በቂ ገንዘብ ለመመደብ እንደማይቻልም ገልጸዋል። ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ዶክተር ምትኩ ወልደሰንበት በበኩላቸው መመሪያው ከተዘጋጀ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ከማጠናከር ባሻገር ከሌሎች ተቋማት ጋር የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንደሚረዳ ተናግረዋል። በዩኒቨርሲቲው የገንዘብ ችግር ባይኖርም የተዘጋጀ መመሪያ ባለመኖሩ ገንዘብ አውጥቶ በመጠቀም ለላቦራቶሪ፣ ለጥናትና ምርምር ስራዎች ለማዋል እንደሚያስቸግር ጠቁመው አሁን መመሪያው ችግሩን እንደሚፈታ እምነታቸውን ገልጸዋል። በኢትጵጵያ 45 የመንግስትና አራት የግል በጥቅሉ 49 ዩኒቨርሲቲዎች ይገኛሉ።                                        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም