በአማራ ክልል በመኸር ወቅት ከለማው መሬት ውስጥ ግማሽ ያህሉ ሰብል ተሰብስቧል

58
ባህርዳር ህዳር 21/2011 በአማራ ክልል በመኽር ወቅት ከለማው መሬት ውስጥ እስካሁን ከሁለት ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሚሆነው ሰብል መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። በቢሮው የሰብል ልማት ባለሙያ ወይዘሮ እንየ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት ሰብሉ የተሰበሰበው ባለፈው የመኽር ወቅት በክልሉ አራት ነጥብ አራት ሚለዮን ሄክታር ከሚጠጋ መሬት በተለያየ ሰብል ለምቷል፡፡ እየጣለ ባለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ጉዳት እንዳያደርስም ህብረተሰቡ እስካሁን ባከናወነው ስራ ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ የለማ ሰብል መሰብሰብ ተችሏል። በደቡብ ጎንደር፣ ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም፣ ደቡብና ሰሜን ወሎ ዞኖች የሚገኙ ትምህርት ቤት ተማሪዎችና መምህራን የደረሱ ሰብሎችን እንዲሰበስቡ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። ሌሎች ነዋሪዎችም በአደረጃጀታቸው መሰረት የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ እየጣለ ከሚገኘው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የመታደግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ባለሙያዋ አስረድተዋል። በቀጣይም አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎች ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሹ  በመሰብሰብ የማዳረቅና የማናፈስ ስራውን ማከናወን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ የደረሰውን ሰብል በሰው ጉልበት ከመሰብሰብ ጎን ለጎን በምስራቅ ጎጃም ዞን በሚገኙ አራት ስንዴ አብቃይ ወረዳዎች 19 ኮምባይነሮችን በመጠቀም በኩታ ገጠም የለማን የስንዴ ሰብል መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ባለፉት 10 ቀናት  ኮምባይነሮችን በመጠቀም  በሁለት ሺህ 356 ሄክታር መሬት የተዘራን የስንዴ ሰብል አጭደው በመውቃት 108 ሺህ 534 ኩንታል ምርት ወደጎተራ መግባቱን አስረድተዋል። በቀጣይም በምዕራብ ጎጃም ዞን ደንበጫና ወንበርማ ወረዳዎች 24 ተጨማሪ ኮምባይነሮች በማስገባት በሁለቱም ዞኖች በ30 ሺህ ሄክታር የተዘራን የስንዴ ሰብል ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን ባለሙያዋ አስረድተዋል፡፡ ቀሪውን  ሰብል  ለመሰብሰብም በየደረጃው የሚገኘው የግብርና መዋቅር ድጋፍና ክትትል እያደረገ እንደሚገኝም አስታውቀዋል። በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ የዳት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሞገስ ሲሳይ ከሳምንት በፊት ይጥል የነበረው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በመቆሙ በአንድ ሄክታር ተኩል መሬት ላይ ያመረቱትን የቢራ ገብስና የባቄላ ሰብላቸውን መሰብሰብ እንደቻሉ ተናገረዋል። በዞኑ የላይ ጋይንት ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አለምነው ውቤ እየጣለ ባለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ምክንያት የደረሰውን ሰብል መሰብሰብ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ በአዊ ዞን አየሁ ጓጉሳ ወረዳ የሚገኙት አርሶ አደር ገደፋው ሞገስ በበኩላቸው የበቆሎ ሰብላቸውን መሰብሰባቸውን ገልጸው  በቀጣይም የስንዴ ሰብላቸውን ለመሰብሰብም እየተዘጋጁ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የታጨደው ሰብል እንዳይበላሽ  የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን አርሶ አደሩ ተናግረዋል፡፡ በአማራ ክልል በ2010/11 የምርት ዘመን በመኽር ከለማው መሬት 110 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ከክልሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም