ከጣና እስከ አባያ ምን ይሰማል?

2041

     በደሳለኝ ካሳ ( ኢዜአ)

ለመጀመሪያ ጊዜ በ17ኛው ክፍለ ዘመን በላቲን አሜሪካ- በብራዚልና አርጀንቲና  እንደተከሰተና ከዚያም ወደ አፍሪካ- ሩዋንዳ በ19ኛው ክፍለ  ዘመን እንደገባ ይነገራል፡፡ ወደ አፍሪካ የገባበት መንገድ ቆሽት የሚያሳርር ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ነገሩ እንዲህ ነው፡፡  የሚያምር አበባ ስላለው የቤልጂየም ቅኝ ገዥዎች ስጦታ በሚመስል መልኩ ነው ያስገቡት፡፡

በሂደትም ከቪክቶሪያ ሀይቅ በመዛመት ከናይልወንዝ ተፋሰስ ወደ ኢትዮጵያ ሳይገባ እንዳልቀረ ይነገራል፡፡

የሆነው ሆኖ በኢትዮጵያ ለመጀሪያ ጊዜ በ1956 ዓ.ም በአቡነ ሳሙኤል ግድብ ላይ መታየቱን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እምቦጭ በሚል መጠሪያ በሚታወቀው ወራሪ አረም እየተጠቃች ነው፡፡ሀይቁ፣ወንዙ፣ግድቡ ሳይቀር  የችግሩ  ሰለባ  ሆኗል፡፡  ጣና፣ አባያ፣ ዝዋይ፣ ባሮ በእምቦጭ አረም ተወረዋል፡፡

ከእምቦጭም ባለፈ ሌሎች  መጤ እጽዋት  የሀገሪቱን  ሀገር በቀል እጽዋት በማመናመን  የስነ ምህዳር መዛባት እያስከተለ ነው፡፡

ከሙያቸው ቅርበት አንጻር ይህን የተመለከቱት አቶ  ኤርሚያስ ማስረሻ  “ኢትዮጵያን ቀርበህ ስታያት  ታሳዝንሃለች፡፡” በማለት  የችግሩን አሳሳቢነት ይገልጹታል፡፡  በርግጥም ጉዳዩ ከማዘንም አልፎ ያማል፤

አቶ ኤርሚያስ ማስረሻ በአካባቢ፣ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን  የደህንነት፣ ህይወትና ወራሪ መጤ ዝርዎች ቁጥጥር ከፍተኛ ባለሙያ ናቸው። ስለ ወራሪው ሃይል እንቦጭ እንዲህ ሲሉም ይገልጻሉ፤ የእንቦጭ አረም በጣና ሐይቅ ላይ በ2003 ዓ.ም ሲከሰት 50ሺ ሄክታር ሸፍኖ ነበር፤ የአካባቢው ህብረተሰብ ባደረገው ጥረት በ2008 ዓ.ም ወደ 20ሺ ሄክታር ዝቅ  ማድረግ  ተችሎ እንደነበር ነው ያስታወሱት።

በተለያዩ የአካባቢው ህብረተሰብና ሌሎች አካላት በተከታታይ በተደረገ ዘመቻ  ባለፈው ግንቦት ወደ 5ሺ 936 ሄክታር ዝቅ ቢልም ዛሬ ላይ ችግሩ ተባብሶ 80 ሺህ ሄክታር መድረሱን ነው ባለሙያው ያወጉን፡፡ በእጅ ለማስወገድ በተደረገው ጥረትም 700ሺ ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር የኦሮሚያ ወጣቶች “ጣና ኬኛ” ብለው በመዝመት አረሙን ለማስወገድ የበኩላቸውን አስተዋጽ አበርክተዋል፡፡ በእንዲህ አይነትቱ በጎ ተግባር መሳተፋቸው ለቀሪው የኢትዮጵ ወጣቶችና ህዝብ መልካም አርዓያ መሆን ይችላሉ ባይ ነኝ።

በቅረቡ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ  የአዲስ  አበባ ወጣቶችን አስታባብረው ወደ  ቦታው በማቅናት  አረሙን  በእጅ  በማስወገድ  ተሳትፎ ከማድረጋቸውም በላይ የአስር ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡

አረሙ በጣና አልተወሰነም እንደ ወረርሽኝ በሽታ ነው አባያ ሀይቅን ስጋት ላይ ጥሎታል ፡፡ በዚህም ህብረተሰቡ የተቻለውን ያህል ለማስወገድ ጥረት ቢያደርግም በዚህ ሃይቅ አረሙን በእጅ ለማስወገድ አዞዎች፣ዘንዶና ጉማሬዎች ስላሉ ለህይወታቸው አደገኛ በመሆኑ የሚያደርጉትን ጥረት ከባድ አድርጎታል። ስጋቱ ቢኖርም ከተወረረው ከ1 ሺ 700 ሄክታር ህብረተሰቡ ባደረገው ጥረት 4 ሔክታር ብቻ ማስወገድ እንደቻለ ነው አቶ ኤርሚስ  የሚናገሩት። ችግሩ በባሮ ወንዝም እየታየ ነው፤ ከተፈጥሮ ሃይቆችና ወንዞች አልፎ ወደ ሰው ሰራሽ ግድቦችም እየተዛመተ ነው፤ የቆቃ ግድብ ለአደጋው ተጋላጭ ሆኗል ይላሉ አቶ ኤርሚያስ።

የሀሮማያ ሀይቅ ተገቢው ጥበቃና እንክብካቤ ስላልተደረገለት  ከአመታት በፊት እንደጠፋ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፤ ብዙዎች የሀረረ ከተማና ሌሎች በዙሪያው ባሉ አካባቢዎች የሚታየውን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግርን  ከሃይቁ መንጠፍ ጋር ያይዙታል፡፡

    ችግሩን ለመከላከል ምን ጥረት ተደረገ?

በአካባቢ፣ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የደህንነት፣ ህይወትና ወራሪ መጤ ዝርዎች ዘርፍ ቁጥጥር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ኤርሚያስ ማስረሻ  እንዳሉት ኮሚሽኑ  የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ጉዳዩ  በቅርበት የሚከታተል የደህንነት ህይወትና ወራሪ መጤ እጽዋት ቁጥጥር ዳይሬክቶሬትን ከስድስት ወር በፊት በአዲስ መልክ አቋቁሟል

ኮሚሽሚኑ ከባለድርሻ አካላትጋር በመተባበር በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተሞክሮዎችን በመቀመር ወራሪና መጤ ዝርያዎችን እንዴት መቆጣጠርና መከላከል እንደሚቻል ፖሊሲ እያዘጋጀ መሆኑንና በቅርቡ ወደ ተግባር ላይ እንደሚውልም ነው አቶ ኤርሚያስ የነገሩን። ኮሚሽኑ ባለፈው አመትለዚሁ ተግባር የሚውል 2.5 ሚሊየን ብርና ቁሳቁስድ ድጋፍ ማድርጉንም ነው የጠቆሙት፡፡

በስነ ህወታዊ የቁጥጥር ዘዴ ለመከላከልም ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ እምቦጭ ብቻ መመገብ የሚችሉ 4 ሺ ጥንዚዛዎች በማምረት ከነዚህ መካከልም 2ሺዎቹ በቅርቡ ወደ ተግባር ለመግባት ዝግጁ ሆነዋል። ጥንዚዛዎቹ ከእንቦጭ ውጭ ሌላ እጽዋት መመገብ ስለማይችሉ በስነምህዳር ላይ የሚያደርሱት ጉዳት እንደማይኖርም ነው ባለሙያው  ያብራሩልን፡፡

ከዚሁጋር በተያያዘ  በኢትዮጵያ አካባቢ ደን ምርምር ተመራማሪ  አቶ አዱኛው አድማስ ጋር ቆይታ አድርገን ነበር። በምርምር ተቋሙ ከ100 በላይ የፈንገስ አይነቶች ተሞክረው 5ቱ ተስፋ ሰጭ ውጤት ማሳየታቸውንም ነግረውናል። ወደ ሃይቁ ሲለቀቁ  በብዝሃ ህይወት ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት በተገቢው ሁኔታ መጠናት ስላለበት ወደ ተግባር ለመግባት በሂት እንደ ሆነም  ነው አቶ አገዱኛ የነገሩን።

ኬሚካል በመጠቀም  ለማስወገድ በላብራቶሪ ተሞክሮ  መልካም ውጤት መታየቱን ያመላከቱት  ተመራማሪው፤ ኬሚካሉን ለማግኘት የሚስፈልገው ወጭ ከፍተኛ ከመሆኑም ባለፈ በአካባቢ ላይ የሚያስከተለው ጉዳትም ስለሚኖር ብዙም ተመራጭ እንዳልሆነ ነው የሚያብራሩት፡፡

በማሽን ለማስወገድ የተደረጉ ሙከራዎች መልካም ቢሆንም ማሽኑ ሲገዛ የመለዋወጫ  ዕቃዎች ታሳቢ ከማድረግ ጀምሮ አጠቃቀሙ በተጠና መንገድ ባለመሆኑ ለብልሽት የሚዳረጉበት ሁኔታ እንደሚያጋጥም ነው  አቶ አዱኛው የነገሩን። አሁን ስራ ላይ ያሉ ሁለት ማሽኖች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ አዱኛው  ማሽኑ ከውሃው ላይ ከማስወገድ  በስተቀር  አረሙን ስለማይፈጩት በእጅ ከማስወገዱ ብዙም  የተለየ  አይደለም ይላሉ።

ከእምቦጭ ባልተናነሰ ጣና ላይ አደጋ የደቀነ ሌላም ችግር አለ ይላሉ  ተመራማሪው፡፡ “ከገበሬው  የእርሻ ማሳ  በየአመቱ በአማካይ ስድስት ሚሊን ቶን ደለል አፈር ወደ ሃይቁ ይገባል፤ ይህ ደግሞ ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ያደርገዋል፡፡ለምን ቢሉ አንድም በቀጥታ ሃይቁ  በሂደት በደለል  ሊሞላ ይችላል፤ ሁለትም ደለሉ በውስጡ የያዘው ንጥረ ነገር ለእምቦጩ ለምግብነት  ተስማሚ በመሆኑ በፍጥነት እንዲራባ ያደርገዋል” በማለት ነው የችግሩን አሳሳቢነት የገለፁት፡፡  በሃይቁ ላይ እቦጭ ለመጀመሪ ጊዜ እንደታየ መከላከል ያልተቻለው የመስፋፋት ባህሪውን ካለማወቅና  በቸልተኝነት ምክንያት መሆኑንም አቶ አዱኛ ሳይጠቅሱ አላለፉም።

እምቦጭ ግን ለምን እምቦጭ ተባለ?

ውሃ ምን ቢወቅጡት እምቦጭ ከማለት ውጭ የሚያመጣው ለውጥ እንደሌለ ሁሉ፡፡ እምቦችጭም ምን ቢነቅሉት እጅ ቢበዛበት አድሮ ቃሪያው ነው፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ባህረውም እምቦጭ እንደተባለ ነው አቶ ኤርሚያስ የሚናገሩት ፡፡ በቅጠሉም፣ በግንዱም ሲለሚራባ ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩትም  ዘሩ ለ28 አመታት ሳይበሰብስ የመቆየት አቅም ስላለው ምቹ ሁኔታ ሲያገኝ በቅሎ መራባት ይጀምራል፡፡ ይሄም ሌላው ራስ ምታት ነው ፤ አስወግጀዋለሁ እፎይ የሚያስብል ነገር የለውምና፤

           እምቦችጭ ጥቅም ይኖረው ይሆን?

በባንግላዴሽ እምቦጭን በተወሰነ ደረጃ ለምግብነትእንደሚጠቀሙበትመረጃዎች ያመላክታሉ፡፡  ደቡብ አፍሪካ ደግሞ እንደዘንቢል ለመሳሰሉ ቁሳቁስ መስሪያነት ይጠቀሙበታል፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባደረገው ጥናትም ኢታኖልና የላብራቶሪ ኬሚካል ማምረት እንደሚቻል በጥናት እንደደረሰበት ከተነገረ ሰነባብቷል። እንደ ናይትሮጂንና ፎስፈረስ የመሳሰሉ ንጥረ ነገሮችን የመጠቀም ባህሪ ስላለው ለማዳበሪነት ሊውል እንደሚችልም  የዘርፉ ባለሙዎች ይናገራሉ፡፡ ይህን መሰርት በማድረግም  ለማዳበሪያነት  ለማዋል ጥናት እየተደረገ መሆኑም ተመራማሪው አመላክተዋል፡፡

አረሙ  በሃይቆቹ ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት በጥቂቱ

‘ አንበሳ ሲያረጅ የዝንብ መዋያ ይሆናል’ እንዲሉ የውሀ መጠን እየቀነሰ ሲሄድ አካባቢው ወደ ረግረጋማነት ይቀየርና እንደ ወባ ትንኝ  ለመሳሰሉ የነፍሳት መራቢ ይሆናል። በሀይቁ ዙሪያ ያሉ የመስኖ ስራዎች ይስተጓጎላሉ፤የአሳምርት ይቆማል፤ በሃይቁ ዳር የነበሩ ለእንስሳት መኖ  የሚውሉ የሳር አይነቶችና ሌሎች እጽዋት ይጠፋሉ። በሀይቁ ላይ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት ይስጓጎላል፡፡ “የኢትዮጵያ 50 በመቶ ውሃ የምታገኘው ከጣና በመሆኑ ጣና ደረቀ ማለቱ በመላሃ ገሪቱ የሚገኙ ውሃማ አካላት ተጽእኖ እንደሚርፍባቸው ነው  አቶ አዱኛው የሚብራሩት፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ሃገሪቱ በድርቅ መመታቷና በረሃማነት መስፋፋቱ  ስለማይቀር “ሳይቃጠል በቅጠል” የሚለውን አባባል አሁን ተግባር ላይ የሚናውልበት ጊዜ ላይ ነን፡፡

ወራሪ መጤ እጽዋት እንዴት  ወደ ሃገር ሊገቡ ይችላሉ?

አቶ ኤርሚያስ እንደሚሉት ወራሪ መጤ ዝርዎች በማወቅና ባለማወቅ ወደ ሃገር ወስጥ ይገባሉ፡፡ ድርቅ መቋቋም የሚችሉ የእጽዋት አይነቶች ሆን ተብሎ ወደ ሃገር የሚገቡበት ሁኔታ መኖሩን ያብራራሉ፡፡

በኢትዮጵያ አካባቢ ደን ምርምር ተመራማሪው አቶ አዱኛው አድማስ  እንደሚሉት ደግሞ መጤ አረሞች ለምርምር፣ የተራቆቱ  አካባቢዎችን መልሶ እንዲያገግም  በሚል ወደ  ሃገር ውስጥ እንደሚገቡ  ነው የነገሩን። ሆኖም እጽዋቱ ወደ ሀገር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ጥቅምና ጉዳታቸውን  በጥናት ለይቶ  የማስገባት ክፍተት  እንደነበረ  ነው የጠቀሱት።

ለአብነትም  በሳይንሳዊ ስያሜው ፕሮስኦፊስ  ወይም የወያኔ ዛፍ የሚባለው በ19 80ዎቹ ገደማ የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ እንዲያገግም  በሚል ሳይገባ እንዳለቀር ነው አቶ አዱኛ  የሚናገሩት፡፡

ዛሬ ላይ ግን ዛፉ በአፋር ክልል በመስፋፋቱ  ምክንያት ሀገር በቀል እጽዋትን  እያመነመናቸውና  እያጠፋቸው ነው፡፡ ይባስ ብሎ  በአዋሽ ብሄራዊ ፓርክ ላይም ቀላል የማይባል ስጋት ደቅኗል ይላሉ፡፡ ዛፉ በብዛት ከመስፋፋቱ  የተነሳ ለመከላከል አስቸጋሪ ደረጃ  ላይ መድረሱን ያመላክቱት ተመራማሪው  ‘የአገሩን በሬ በአገሩ ሰርዶ’ እንዲሉ የአካባበው ህብረተሰብ ለከሰል ምርት መጠቀም ስለጀመረ   በሂደትም  መስፋፋት ሂደቱን  ለመግታት እንደሚያስችል ተስፋ አለ ይላሉ።

በሳይናሳዊ መጠሪያው ላንታና ላማራ በአገርኛ ስያሜው የወፍ ቆሎ የተኘው መጤ እጽዋትም  እንደወያኔ ዛፍ ሁሉ የተራቆተን አካባቢ መልሶ እንዲያገግም  በሚል ከውጭ ሀገር እንደገባና  አሁን ላይ  በመላ ሀገሪቱ  ተሰራጭቶ  ለመከላከልም  ከቁጥጥር ውጭ መሆኑን ተመራማሪው ይናገራሉ፡፡ የአረሶ አደሩን  የእርሻ  ማሳ በመውረርም   በግብርና ስራ ላይ ችግር እያስከተለ ነው ይላሉ፡፡ እሾሃማ ተክል በመሆኑም  ምንም  ጠቀሜታ የለውም፤ ለማገዶ ፍጆታም  እንደማይውል ነው የጠቀሱት። እነዚህን እጽዋት አርሶ አደሮች  የእርሻ መሬታቸውን ሲወርባቸው  ለማስወገድ ከሚደረጉት ጥረት ውጭ በሚለከተው አካል  ችግሩን ለመከላከል የተሰራ ስራ አለመኖሩን  ያብራራሉ፡፡ ኢትዮጵያ 35 በላይ መጤ ዝርያዎች መኖራቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ታዲያ ለበጎ ተብሎ ወደ ሃገር ገብተው እንዲህ አይነት የከፋ ችግር የሚያስከትሉ ከሆነ ሌላ ተጨማሪ እጽዋትም እንዳይወረን የሁሉም ትኩረትና እገዛ ያስፈልጋል እያልን የዘርፉ ባለሙያዎችም ያላቸውን እውቀት ተጠቅመው ሀገራችንን ስነ ምህዳር ያንዣበበትን አደጋ ሊታደጉ ይገባል እንላለን።  ሠላም!