የዘመናዊ ንብ ቀፎ ዋጋ በመወደዱ ገዝተን መጠቀም አልቻልንም - የማእከላዊ ጎንደር ዞን አርሶ አደሮች

448
ጎንደር ህዳር 21/2011 የዘመናዊ ንብ ቀፎ ዋጋ ከአቅም በላይ በመሆኑ ገዝተን መጠቀም አልቻልንም ሲሉ በንብ ማነብ ስራ የተሰማሩ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አርሶ አደሮች ቅሬታቸውን ገለፁ፡፡ የዞኑ እንስሳት ሀብት ልማት ተጠሪ ጽህፈት ቤት በበኩሉ ንብ አናቢዎች ዘመናዊ የንብ ቀፎ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከ3ሺ በላይ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች በብድር የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻችት እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የወገራ ወረዳ ነዋሪ አርሶአደር መላኩ ምትኩ ለኢዜአ እንደተናገሩት ዘመናዊ የንብ ቀፎ የማር ምርት እንደሚጨምር ግንዛቤው ቢኖረኝም ዋጋው ከአቅም በላይ በመሆኑ ገዝተው መጠቀም አልቻሉም፡፡ አርሶ አደር መላኩ እንዳሉት ቀደም ሲል 500 ብር ይገዙት የነበረው አንድ ዘመናዊ የንብ ቀፎ በአሁኑ ወቅት በሶስት እጥፍ ጨምሯል፡፡ ''ሁለት ዘመናዊ ቀፎዎች አሉኝ ሆኖም ተጨማሪ ሁለት ቀፎ ገዝቼ የማር ምርቴን ለማሳደግ ብፈልግም የዋጋው መወደድ ፍላጎቴን ገቶታል'' ብለዋል፡፡ በምእራብ ደንቢያ የጩሃይት ከተማ ነዋሪ አርሶአደር ግዛት ሞላልኝ በበኩላቸው ከባህላዊ ቀፎ የማገኘው የማር ምርት ዝቅተኛ በመሆኑ ዘመናዊ ቀፎ ገዝቼ ለመጠቀም ፍላጎቱ ቢኖረኝም በዋጋው መወደድ ተጠቃሚ መሆን አልቻልኩም፡፡ መንግስት በረዥም ጊዜ ክፍያ ብድር ፈቅዶልን ዘመናዊ የንብ ቀፎ የምናገኝበት ሁኔታ ሊያመቻችልን ይገባል ሲሉም ንብ አናቢ አርሶአደሮቹ ጠይቀዋል፡፡ የዞኑ እንስሳት ሀብት ተጠሪ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር ይበልጣል ተረፈ ዘመናዊ የንብ ቀፎ ለማር ምርታማነት ማደግ አስተዋጽኦ እንዳለው ቢታመንም የዞኑ ንብ አናቢ አርሶአደሮች ዘመናዊ የንብ ቀፎ ገዝቶ የመጠቀም ተሳትፏቸው ዝቅተኛ ነው፡፡ ከአንድ ዘመናዊ የንብ ቀፎ እስከ 20 ኪሎ ግራም የማር ምርት ማግኘት ይቻላል የሚሉት ሃላፊው አርሶአደሩ ከሚጠቀምበት ባህላዊ ቀፎ ጋር ሲነጻጸርም በሶስት እጥፍ የምርት ጭማሪ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ በዞኑ ከፍተኛ የንብ ሀብት ባለባቸው በወገራ፣ በምእራብና ምስራቅ በለሳ እንደሁም በኪንፋዝ በገላና በጠገዴ ወረዳዎች ባለፈው ዓመት ከ4ሺ በላይ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን ለማሰራጨት ቢታቀድም የተሰራጨው ከ400 እንደማይበልጥ  ገልፀዋል፡፡ አርሶአደሩን የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ሞዴል የንብ ሰርቶ ማሳያዎችን ከማስተዋወቅ ጀምሮ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን በረጅም ጊዜ ብድር የሚያገኝበትን አሰራር ለመዘርጋት ከአጋር አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የወገራ ወረዳ እንስሳት ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አንዳርግ አለባቸው በበኩላቸው በወረዳው የተመረተ 1ሺ 500 የንብ ቀፎ ገዢ በማጣት ካለፈው አመት ጀምሮ ሳይሰራጭ መቀመጡን አስታውቀዋል፡፡ ንብ አናቢዎችን ለማበረታታት ሲባል የንብ ቀፎው ከተመረተበት 2ሺ 900ብር ወደ 1ሺ 760 ብር ዝቅ በማድረግ አርሶአደሩ እንዲገዛ ሁኔታዎች ቢመቻቹም አርሶአደሩ እጅ በእጅ ለመግዛት ፍቃደኛ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎቹ ከአንድ እስከ ሁለት አመት ለሚሆን ጊዜ ጥቅም ሳይሰጡ ያለስራ መቀመጣቸውን ጠቁመው፤ አሁን ላይ በረጅም ጊዜ ብድር ለመስጠት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡ በዞኑ በያዝነው አመት ከ2ሺ ቶን በላይ የማር ምርት ለገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ሲሆን ባለፈው ጥቅምት ወር ብቻ 450 ቶን የማር ምርት ለገበያ ማቅረብ ተችሏል፡፡ በማእከላዊ ጎንደር በንብ ማነብ ስራ ከተሰማሩ 10ሺ አርሶአደሮች መካከል የዘመናዊ የንብ ቀፎ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ400 እንደማይበልጥ ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም