በኢትዮጵያ ለንፋስ ኃይል ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የሚውል 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ከዴንማርክ ተገኘ

154
አዲስ አበባ ግንቦት 16/2010 ለአሰላ የንፋስ ኃይል የኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት የሚውል 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ከዴንማርክ መንግስት ተገኘ። ከተገኘው ብር ውስጥ 2 ነጥብ 7 ቢሊዮኑ በእርዳታ የተሰጠ ሲሆን ቀሪው በአነስተኛ የወለድ መጠን የተሰጠ ብድር እንደሆነ ተጠቁሟል። በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ሚሲስ መቴ ቲግሰን እና በኢትዮጵያ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አድማሱ ነበበ መካከል የስምምነት ፊርማው ተካሂዷል። አምባሳደሯ እንደገለጹት፤ ዴንማርክ የአሰላ የንፋስ ኃይል የኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክትን የፋይናንስ ወጪ የምትደግፈው ከታዳሽ ኃይል የሚመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለማሳደግ ነው። ኢትዮጵያ ተስማምታ የተቀበለቻቸውን የዘላቂ ልማት ግቦች ለማሳካትና እ.አ.አ በ2025 የዜጎች የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ዕቅዱ እንዲሳካ ዴንማርክ ድጋፏን እንደምትቀጥል ገልጸዋል። ዴንማርክ የምትጠቀመው የኤሌክትሪክ ኃይል ግማሹ ከንፋስ ኃይል የሚገኝ መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደሯ ኢትዮጵያም የታዳሽ የኃይል ምንጭ ባለቤት ለመሆን እያደረገች ያለውን ጥረት አገራቸው ለመደገፍና በዘርፉ ያላትን ልምድ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ በበኩላቸው የዴንማርክ መንግስት ለፕሮጀክቱ ግንባታ ላደረገው የገንዘብ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። 'በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት ካለው የገንዘብ እጥረት አኳያ እርዳታውና ብድሩ እጥረቱን በመቅረፍ ረገድ እገዛ ይኖረዋል' ብለዋል። የአሰላ የንፋስ ኃይል የኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት በአራትና በአምስት አመታት ጊዜ ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሎ እንደሚገመት ጠቁመዋል። የዴንማርክ ድጋፍ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን መጨረሻ ከንፋስ ኃይል ኤሌክትሪክን ለማመንጨት የተቀመጠውን ግብ ከማሳካት አኳያ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ ከንፋስ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር 100 ሜጋዋት የማመንጨት አቅም ይኖረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም