ለወጣቶች የመስሪያ ቦታ እጥረትና የገበያ ትስስር አለመፈጠሩ በስራቸው ላይ ጫና እየፈጠረባቸው ነው

69
አዲስ አበባ  ህዳር 21/2011 በወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ የተደራጁ የአዲስ አበባ ወጣቶች የመስሪያ ቦታ አለመኖርና የገበያ ትስስር አለመፈጠር በስራቸው ላይ ጫና እንደፈጠረባቸው ገለጹ። ወጣት ተፈሪ እሱባለው በተመረቀበት የምህንድስና ሙያ ተመያሳሳይ ሙያ ካላቸው ጓደኞቹ ጋር በህንጻ ማጠናቀቅ ስራ ተደራጅተው ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ከተመደበው ተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ 200 ሺህ ብር ተበድረው በ2008 ዓ.ም  ወደ ስራ ገብተዋል። ወጣት እሱባለው እንደሚናገረው፤ በህንጻ ማጠናቀቅ የተጀመረውን ስራቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በራሳቸው ተጫርተው የመስራት ህልም አላቸው። ወደ ስራ ከገቡ ጀምሮ ስራው ቀጣይነትና ግልጽ ጨረታ አለመኖር፣ የመስሪያ ቦታ እጥረት ህልማቸው እውን እንዳይሆን ስጋት እንዳሳደሩባቸው በመግለጽ የሚመለከተው አካል ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተናግሯል። ሌላው ስራ ፈጣሪ ወጣት ሰለሞን አሉላ በተመሳሳይ ከጓደኞቹ ጋር በህትመትና ማስታወቂያ ስራ ከሁለት አመት በፊት 240 ሺህ ተበድረው ስራ እንደጀመሩ ይናገራል። እውቀታቸውን ወደ ስራ የሚቀይሩበት ገንዘብ በማግኘታቸው ደስተኛ ሆነው ወደ ስራ ቢገቡም የመስሪያ ቦታ አለመመቻቸት አሁንም ድረስ ፈተና እንደሆነባቸው ነው የተናገረው ። ከአንድ ወር በፊት በምግብ ዝግጅት ብድሩን በመጠቀም ወደ ስራ የገቡት ፍቅርተ ዳዊትና ጓደኞቿ በብድር መስጠት ላይ መዘግየት እንደሚታይ በመጠቆም ቀጣይ ለሚደራጁ ወጣቶች አሰራሩ መስተካከል እንዳለበት ጠቁማለች። በአዲስ አበባ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ የወጣቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ቡድን መሪ አቶ ሙላቱ አበበ ወጣቶች ያነሱት የመስሪያ ቦታ ችግር ትክክል ስለመሆኑ አረጋግጠዋል። የገበያ ትስስር ላይም እንዲሁ ያለው ችግር ትክክል መሆኑን በመግለጽ ችግሩን መንግስት እየፈታ ሊቀጥል የማይችል በመሆኑ ወጣቶችም የመፍትሄ አካል ለመሆን መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል። ከመስሪያ ቦታ ጋር የተነሳውን ችግር ለመፍታት የመስሪያ ኦዲት በማድረግ ለመፍታት እንደሚሞከር ገልጸዋል። በፍጥነት አያጠናቅቁም በሚል ስጋት ለአዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ስራዎችን አለመስጠት ና ክፍያ በወቅቱ አለመፈጸም ችግር እንዳለም አንስተዋል። ብድር ወስደው መጥፋት፣ አዳዲስ ስራ ፈጣሪዎን ስራ አለመስጠት፣ የተናበበ ስራ አለመኖር፣ ወጥ መመሪያ አለመኖር የስራ ዕድል ፈጠራ እንቅስቃሴው ፈተና ነው። ለአዲስ አበባ ከተማ መንግስት ከመደበው 10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ ውስጥ 419 ሚሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን ይህንንም ሙሉ ለሙሉ ለወጣቶች ማበደር ተችሏል። እስካሁን ድረስ 65 ሚሊዮን ብሩ ተመላሽ ሆኗል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም