የዜጎች ሰብዓዊና ህገ መንግስታዊ መብት ጥሰው የሚሰጣቸውን ምክረ ሃሳብ የማይተገብሩ ተጠያቂ ይሆናሉ-የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን

65
አዲስ አበባ  ግንቦት 16/2010  በዜጎች ሰብዓዊና ሕገ መንግስታዊ መብት ላይ ጥሰት ፈጽመው የሚሰጣቸውን የማስተካከያ ምክረ ሃሳብ ተግባራዊ የማያደርጉ አካላት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጠየቁ አደርጋለሁ ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለጸ። የኮሚሽኑ ሰራተኞች 27ኛውን የግንቦት ሃያ የድል በዓል በፓናል ውይይትና በተለያዩ ዝግጅቶች ዛሬ አክብረዋል። ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በሆኑ የማይደፈሩና የማይገሰሱ፣ በህይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነጻነት መብት እንዳለው በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ተደንግጓል። ኮሚሽነሩ ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር ለኢዜአ እንዳሉት ኮሚሽኑ ባለፉት 12 አመታት የስራ ዘመኑ እነዚህን የህገ መንግስት ምንነትና ድንጋጌዎችን ለህብረተሰቡ ለማሳወቅ ሰርቷል። የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለባቸው በሚባሉ ማረሚያ ቤቶች፣ ፖሊስ ጣቢያዎችና ሌሎች ተቋማት ላይ ክትትል በማድረግ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱ በማድረግም እንዲሁ። "ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ተጠያቂነትን አረጋግጠናል ብለን አንወስድም" ያሉት ዶክተር አዲሱ ተጠያቂነትን በማረጋገጥ በኩል ብዙ መስራት እንደሚጠይቅ ነው የገለጹት። እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ በተጠያቂነት በኩል ለህግ መቅረብ ያለባቸው ወደ ህግ ለማቅረብና ዜጎች ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ብዙ መስራት ይጠይቃል። በመሆኑም የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የጣሱ አካላት በህግ እንዲጠየቁ በማድረግ የማይፈጽሙ ተቋማትንና ሃላፊዎችን ዝርዝር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማስተላለፍ ተጠያቂ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። የተቋሙ ሰራተኞችም የኮሚሽነሩን ሃሳብ በመጋራት በምርመራ የተገኙ የመብት ጥሰቶች ውሳኔ የማይፈጽሙ አካላት ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ነው አስተያየት የሰጡት። ኮሚሽነሩ ግጭት የሚያስከትለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በዘላቂነት ለመፍታትም በጥናት ላይ የተመሰረተ ምክረ ሃሳብ ለመንግስት ለማቅረብ እየሰራ ነው ብለዋል። በበዓሉ ላይ በአገሪቷ በሰብዓዊ መብት ማስከበር የመጡ ለውጦችና አሁንም ትኩረት የሚያሻቸው ጉዳዮች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም