የመማሪያ መፅሃፍትን በሞባይል ስልክ ላይ ማግኘት የሚያስችል መተግበሪያ ስራ ላይ ዋለ

175
አዲስ አበባ ህዳር  21/2011 የመማሪያ መፅሃፍትን በሶፍት ኮፒ አውርዶ መጠቀም የሚያስችል የሞባይል መተግበሪያ ስራ ላይ ማዋሉን የአዲስ አበባ መገናኛና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ኤጀንሲ አስታወቀ። ከዛሬ ጀምሮ ስራ ላይ የዋለው መተግበሪያው የ8ኛ እና 10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናዎችን ውጤት መመልከት የሚያስችልም ነው። የኤጀንሲው ኃላፊ ዶክተር አብዮት ባዩ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ የሞባይል ስልኮች በስፋት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑ መተግበሪያውን ወላጆችም ሆኑ ተማሪዎች እንዲጠቀሙበት አስተዋፅኦ ያደርጋል። ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል በማስተማሪያነት ስራ ላይ ያሉ መፃህፍት በመተግበሪያው ላይ የተጫኑ በመሆኑም በቀላሉ በማውረድ መጠቀም ይችላሉ። በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የአይሲቲ ዳይሬክተር አቶ የኔጌጥ በለጠ መተግበሪያው መምህራን ባሉበት ቦታ ሆነው ለማስተማር ስራቸው እንዲዘጋጁ እድል እንደሚፈጥርላቸው ገልጸዋል። በግል ትምህርት ቤቶች መፃህፍት በነጻ የማይታደል በመሆኑ መተግበሪያው ጥሩ አማራጭ እንደሚሆንም ተናግረዋል። ተማሪዎች ካሉበት ክፍል በተጨማሪ ያለፉትንና በቀጣይ የሚማሩበትን መፅሃፍ ማግኘት ስለሚያስችላቸውም ለዝግጅት ይረዳቸዋል። በሌላ በኩል መተግበሪያው መጻህፍትን ከማውረድ በተጨማሪ አገር አቀፍ የፈተና ውጤት ማየት የሚያችል ሲሆን በቀጣይም ለ8ኛ ክፍል ተማሪዎች የቆዩ ሞዴል ፈተናዎችን ለማካተት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። መተግበሪያው ማሻሻያ ተደርጎበት ለመምህራን ብቻ የይለፍ ቃል በመስጠት ደጋፊ መፃህፍትና መመሪያዎችን ተደራሽ ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝም አቶ የኔጌጥ ጠቁመዋል። ይህ መተግበሪያ ተማሪዎች በሞባይል ስልኮች ጌሞችና ሌሎች አላስፈላጊ ነገሮችን በማየት ጊዜያቸውን ከማባከን ይልቅ መጽሃፍትን የማንበብ ባህል እንዲያዳብሩ በር ይከፍታል ሲሉ አክለዋል። መጽሃፍቱን ለማውረድ በቅድሚያ ጉግል ፕሌይ ላይ በመግባት በእንግሊዝኛ 'addis ababa education bureau' ብሎ በመፈለግ መተግበሪያውን ማውረድ እንደሚቻል ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም