ቤኒን እና ሲሼልስ ከአፍሪካ ክፍት የቪዛ አገልግሎት በመስጠት ቀዳሚ ሆኑ

169
ህዳር 21/2011 ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ቤኒን የአፍሪካ ሃገራት ዜጎች ወደ አገሯ ጉዞ ሲያደርጉ ይጠየቁ የነበረውን ቪዛ የሚያስቀር ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ቀዳሚ ስትሆን ሲሼልስ ተከታዩን ደረጃ ይዛለች፡፡
የ2018 የአፍሪካ ክፍት ቪዛ ሪፖርት እንደሚያሳየው ሁሉም የአፍሪካ ሃገራት ዜጎች ያለ ቪዛ ወደ አገሯ መግባት እንዲችሉ በመፍቀድ ቤኒን ቀዳሚ ሆናለች፡፡
ደረጃውን ያወጡት የአፍሪካ ህብረት እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ካለፉት ሶስት ዓመታት ጀምሮ የአፍሪካ አገራት አንዳቸው ለሌላቸው ድንበራቸው ክፍት እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ም/ሊቀመንበር ክዋሲ ካርቲይ ኢትዮጵያ የመዳረሻ ቪዛ መስጠት መጀመርዋ በቀጠናው ነፃ አህጉራዊ የሰዎች ዝውውር እውን ለማድረግ ይረዳል ብለዋል፡፡
ሲሸልስ እና ቤኒን ሙሉ ለሙሉ ለአፍሪካውያን ቪዛ ክፍት በማድረግ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ሲይዙ፤ ሩዋንዳ፣ቶጎ፣ጊኒ ቢሳዉ ፤ኡጋንዳ፣ጋና፣ኬፕ ቨርዲ፤ ኬንያ እና ሞዛንቢክ በቅደም ተከተል ከሶስተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ ይይዛሉ፡፡
ሪፖርቱ በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ዜጎች ወደ 25 ከመቶ የአፍሪካ አገራት ያለ ቪዛ መሄድ እንደሚችሉ የሚያሳይ ሲሆን በፈረንጆች 2017 ይህ አሃዝ 20 ከመቶ እንደነበር ተገልጿዋል፡፡
24 ከመቶ የአፍሪካ አገራት በመዳረሻ ቪዛ አማካኝነት የአፍሪካ ዜጎች ወደ አገራቸው የሚያስገቡ ሲሆን 51 ከመቶ የአፍሪካ አገራት የሌሎች ዜጎችን የሚቀበሉ በቪዛ መሆኑንም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
ምንጭ፡አፍሪካ ኒውስ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም