የባህር ዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ፈጽመዋል ያላቸውን አምስት ተከሳሾች እስከ እድሜ ልክ በሚደርስ ጽኑ እስራት ቀጣ

48
ባህርዳር ህዳር 20/2011 የባህር ዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ፈጽመዋል ባላቸው አምስት ተከሳሾች ላይ ከ20 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ በሚደርስ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ። የፍርድ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አለምሸት ምህረቴ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በተከሳሾች ላይ የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው የባህርዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ህዳር 18 ቀን 2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት ነው። ''1ኛ አንማው ይርዳው፣ 2ኛ ከድር ሙሀመድ፣ 3ኛ ሰሎሞን ሙሉነህ፣ 4ኛ መሰረት ታከለና 5ኛ ነፃነት ታከለ በተባሉ ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔውን ያሳለፈው እስማኤል አህመድ የተባለውን ግለሰብ ታህሳስ 24 ቀን 2009 ዓ.ም መግደላቸው በአቃቤ ህግ በቀረበ ማስረጃ በመረጋገጡ ነው'' ብለዋል። 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች አስቀድመው በነበራቸው የንግድ ውድድር ሟች ለደንቦኞች የዘይት ዋጋ ቀንሶ ይሸጥ ስለነበር ለምን ቀንሰህ ትሸጣለህ እያሉ ሟችን እንደሚያስገድሉት ሲዝቱበት እንደቆዩ የፍርድ ውሳኔ ዝርዝሩ ያስረዳል። በዚህም መሰረት 1ኛ፣ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች የመከላከያ ሰራዊት ልብስ በመልበስና የጦር መሳሪያ በመያዝ ኮማንድ ፖስት ነን ብለው ሟችን በግምት ከምሽቱ 2 ሰዓት አካባቢ ከቤቱ በማስወጣት ጥይት ተኩሰው መግደላቸው ታውቋል፡፡ እንዲሁም የማይገባቸውን የመከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብስ በመልበስ ወንጀል በመፈፀማቸውም በተከሳሾች ላይ የምዕራብ ጎጃም ዞን ፍትህ መምሪያ ባህርዳር ምድብ ዓቃቤ ህግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ክስ መመስረቱን ገልፀዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ከ1ኛ እስከ 4ኛ የሚገኙ ተከሳሾች ድርጊቱን አልፈፀምንም፣ ጥፋተኛም አይደለንም ብለው ክደው ቢከራከሩም አቃቤህግ ያቀረባቸውን ማስረጃዎች ማስተባበል ባለመቻላቸው ቅጣቱ ተላልፎባቸዋል። አምስተኛ ተከሳሽ ነፃነት ታከለ ደግሞ ህጉ በሚያዘው መሰረት ጥሪ ተደርጎለት ሊቀርብ ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ በሌለበት ጉዳዩ ሲመለከት ከቆየ በኋላ በአምስቱም ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱም የአቃቤ ህግንና የተከሳሾችን የቅጣት አስተያየት ተቀብሎ ከመረመረ በኋላ በከባድ የሰው መግደል ወንጀል ፈፅመዋል በማለት ተከሳሾችን ያርማል፣ ያስተምራል፣ ሌሎችንም ያስጠነቅቃል ብሎ ያመነበትን ውሳኔ አሳልፏል። በዚህም 1ኛና 4ኛ ተከሳሾች በ20 ዓመት ፅኑ እስራት፣ 3ኛ ተከሳሽ በ23 ዓመት ፅኑ እስራት፣ እንዲሁም 2ኛና 5ኛ ተከሳሾች ደግሞ በዕድሜ ክል ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ መወሰኑንም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም