ፓርኮቹ የኢኮኖሚ ሽግግር ከማፋጠን ባለፈ የዜጎችን ተጠቃሚነት እንደሚያሳድጉ ተገለጸ

76
አዲስ አበባ  ግንቦት 16/2010 እየተገነቡ ያሉ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የኢኮኖሚውን ሽግግር ከማፋጠን ባለፈ የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንደሚያሳድጉ ተገለጸ። ባለፉት ዓመታት መንግስት በገበያ ትስስር መላላት አርሶ አደሩ ምርቱን በርካሽ ዋጋ እንዲሸጥ የሚያስገድደውን ችግርን ለመፍታት የወሰዳቸው እርምጃዎች በቂ መፍትሄ ሳያመጡ ለዘመናት ቆይተዋል። እንዲሁም በመሰረተ ልማት እጦትና በደላሎች አላስፈላጊ ድርድር ተመርተው ለገበያ ሳይበቁ የተባለሹ ምርቶች በርካቶች ነበሩ። በስራ ዕድል ዕጦት ከቀያቸው ተፈናቅለው ወደ መሃል ከተማ የሚሰደዱ ወጣቶችም ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ይነገራል። መንግስት ችግሩን ለመፍታት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ሥፍራዎች በመለየት ወደ ግንባታ ተሸጋግሯል። የቀድሞ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መብርሃቱ መለስ እንደሚሉት የፓርኮቹ ግንባታ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ በመሆኑ ተመጣጣኝ ዕድገት እንዲኖር ያስችላሉ፡፡ በተለይ የከተሞችን የተቀናጀ ዕድገት ከማፋጠን፣ ለዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በመፍታት የዜጎችን ተጠቃሚነት ያጎለብታል ብለዋል። ኢንዱስትሪ ፓርኮች በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ሥፍራ የሚያቀርቡ መሆናቸውና ተገቢ መሰረተ ልማት የሚገነባላቸው በመሆኑ የአርሶ አደሮችን የገበያ እጦች ችግር በቅርበት ይፈታሉ ይላሉ። አገሪቱ ያላትን ዕምቅ ኃብት ጥቅም ላይ ለማዋል ታስቦ በ2009 ዓም በተጠናው ጥናት ቀድሞ የነበረው የኢንዱስትሪ ዞን ከሌሎች ችግሮች ባሻገር የከተሞች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ ክፍተት እንዳለበት ተስተውሏል። መንግስት ችግሩን ለመፍታት በአራቱ ዋና ዋና ክልሎች ኢኮኖሚያዊ አዋጭነታቸው ተጠንቶ ወደ ግንባታ የገቡና ወደ ስራ ለመግባት የባለሃብቶች ምዝገባ የተጀመረባቸው የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርኮች ተግባራዊ ማድረጉን ገልጸዋል። የክልሎች ኢንዱስትሪ ማዕከላት እየተፈጠሩ በሄዱ ቁጥር ከተሞች በዚያው መጠን እያደጉ የህብረተሰቡ የኑሮ ደረጃ እየተቀየረ፣ እንደሚሄድ ነው ዶክተር መብርሃቱ የተናገሩት። በተጨማሪም በፓርኮቹ አካባቢ አነስተኛ ከተሞች ከመፈጠራቸው ጋር ተያይዞ በአካባቢው መሰረተ ልማት በማሟላቱ ከተሞች ያድጋሉ፤ የህብረተሰቡም ህይወት ይለወጣል ነው ያሉት። እየለሙ ያሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዘመኑ የደረሰባቸውን የግንባታ ሂደትን የተከተሉ በመሆናቸው ከአካባቢ ብክለት የፅዱ ናቸው። ከዚህም ባሻገር ተረፈ ምርታቸውን እንደገና መጠቀም የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙላቸው በመሆናቸው የሃብት ብክለትን ይቀንሳሉ። በቀጣይ አርሶ አደሩ ስለ ማምረቱ እንጂ ስለ ገበያ ማፈላለግ የማያስብበት ስርዓት እንደሚፈጠርም ጠቁመዋል። የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርኮቹ በአራት ክልሎች በ5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የተገነቡ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል ቡልቡላ፣ በአማራ ክልል ቡሬ፣ በደቡብ ክልል ይርጋለምና በትግራይ ክልል ሁመራ አካባቢዎች ይገኛሉ። የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ምግብና ምግብ ነክ የሆኑ ምርቶችን የሚያቀነባብሩ ፋብሪካዎች የሚገነቡባቸው ሲሆን እያንዳንዱ ፓርክ በቀጥታ ለ419 ሺህ፤ በተዘዋዋሪ ደግሞ ለ210 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ግንባታቸው ሲጠናቀቅ የሚያስፈልጋቸው የግብርና ምርት፣ ሳይስተጓጎል በጥራትና በብዛት ማምረትና ማቅረብ እንዲቻል ስትራቴጂክ ዕቅዱ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም