በህፃናት ላይ የሚደርሰውን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለመከላከል የህብረተሰቡ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል-የህጻናት ፓርላማ አባላት

182
ሰቆጣ ህዳር 20/2011 በዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በህፃናት ላይ የሚደርሰውን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ የበኩሉን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ተጠየቀ፡፡ "ህጻናት እንዲማሩ ለችግር እንዳይጋለጡ እና እምቅ ችሎታቸውን እንዲያከብሩ እንደግፋቸው" በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ13ኛ ጊዜ የሚከበረውን የህፃናት ቀን  በፓናል ውይይት ተከብሯል፡፡ በዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የህፃናት ፓርላማ አባላት ለኢዜአ እንደገለጹት በህጻናት ላይ የሚደርሰውን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል፡፡ በሰቆጣ ዋግ ስዩም አድማሱ ወሰን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ9ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው  ዳግማዊት ሀደሩ እንደገለጸችው  "በህፃናት ላይ የሚደርሰውን ጎጅ ልማዳዊ ድርጊት ለመከላከል እየሰራን ነው" ብላለች፡፡ በትምህርት ቤታቸው በተቋቋመው የህፃናት ፓርላማ በአፈ-ጉባኤነት  እያገለገለች መሆኗን የጠቀሰችው ተማሪ ዳግማዊት ፓርላማቸው  በህፃናት ላይ የሚደርሰውን የጎጅ ልማዳዊ ድርጊት ተፅዕኖ አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ይሰጣል፡፡ ''ህፃናት በተለያዩ ጥቃቶች ምክንያት ለከፋ ችግር ይጋለጣሉ'' ያለችው  ተማሪዋ ይህንን ችግር ለማስቀረት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰሩ መሆኑን ጠቁማለች፡፡ በችግር ምክንያት ከትምህርት ገበታ የሚርቁ ህፃናት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የትምህርት ቁሳቁስን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግራለች፡፡ በደሃና ወረዳ የአምድ ወርቅ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪ እጹብ ድንቅ ሹመት  በበኩሉ ህፃናት ባሉበት አካባቢ መብታቸውን እንዲያስከብሩ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ እየሰሩ መሆኑን አመልክቷል፡፡ ወደ ትምህርት ቤት ያልገቡ ህጻናትን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ ህፃናት የተረጋጋ ህይወት ኑሯቸው  በሃገር ተረካቢነት መንፈስ እንዲያድጉ የማድረግ ስራ በህፃናት ፓርላማ  እየተሰራ መሆኑን ተማሪ እጹብ ድንቅ አመልክቷል፡፡ በህፃናት የሚደርሰውን ያለዕድሜ ጋብቻና  መሰል ተፅዕኖዎች ለማስቆም ህብረተሰቡም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ተማሪ  እጹብ ድንቅ ጠቁሟል፡፡ በዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ዝና ጌታቸው  በሁሉም ወረዳዎች የህፃናት ፓርላማ መቋቋሙን ተናግረዋል፡፡ ''ከጎጅ ልማዳዊ ድርጊት አስወጋጅ ጥምረት ኮሚቴ ጎን ለጎን የህፃናት ፓርላማ አስተዋዕፆ እያበረከተ ነዉ'' ያሉት ኃላፊዋ  በ2010 ዓ.ም ብቻ በህፃናት ፓርላማ ጥቆማ 28 ያለአቻ ጋብቻዎች እንዲቋረጡ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡ በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከ14 ሺህ በላይ ህፃናት በችግር ላይ እንደሚገኙ የጠቆሙት ኃላፊዋ አርሶ አደሩ፣ የመንግስት ሰራተኛውና ባለሃብቱ ድጋፉን እንዲያደርግ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ከመንግስት ሰራተኛው ወርሃዊ ደመወዝ ላይ አንድ በመቶ ተቆራጭ በማድረግ 251 ህጻናት በየወሩ ከ250 እስከ 750 ብር ድረስ ቀጥታ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው፡፡ በዘንድሮው አመት በገንዘብ እጥረት ምክንያት ትምህርታቸውን ሊያቋርጡ ለነበሩ 1 ሺህ 758 ህጻናት በ300 ሺህ ብር ወጭ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡ በህፃናት ላይ የሚደርሰውን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት እና ከተፅእኖ ነፃ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ባለሃብቱና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሊደግፉ እንደሚገባ  ኃላፊዋ  አሳስበዋል። በውይይት መድረኩ  በየደረጃው የሚገኙ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ የስራ ኃላፊዎች፣ የህጻናት ፓርላማ አባላት፣ መምህራን እና በዘርፉ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተሳታፊ ነበሩ፡፡   ---END---
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም