ወደ መቅደላ አምባ ተራራ የሚወስደው መንገድ በመበላሸቱ ጎብኝዎችን ማስተናገድ አልተቻለም

132
ደሴ ህዳር 20/2011 በደቡብ ወሎ ዞን ወደ መቅደላ አምባ ተራራ የሚወስደው መንገድ በመበላሸቱ ጎብኝዎችን ለማስተናገድ መቸገሩን የሰላምጌና መቅደላ አምባ የኢኮ ቱሪዝም ማኅበር አስታወቀ፡፡ የማኅበሩ ኃላፊ አቶ ጌትነት አባይ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት ከተንታ ከተማ እስከ መቅደላ አምባ ያለው የ17 ኪሎ ሜትር ጥርጊያ መንገድ በጎርፍ የተቦረቦረና ከተራራ በሚናድ ቋጥኝ የተዘጋ በመሆኑ ለተሽከርካሪ እንቅስቃሴ አዳጋች ሆኗል ። መንገዱ በመበላሸቱ የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎችን ወደ መዳረሻው ማስገባት አለመቻሉን ተናግረዋል። ከአስር አመት በፊት የክልሉ ገጠር መንገድ ባለስልጣን መንገዱን በአፓልት ለማንጠፍ ቃል ቢገባል ተግባራዊ ሳያደርግ መቅረቱን አስታውሰዋል፡፡ ለአምባው የተሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ በ2000 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ሃውልት ሳይሰራ አስር ዓመት እንደሞላው ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል ። የአጼ ቴዎድሮስ የመቃብር ስፍራና የታላቁ ሴባስቶፖል መድፍም የመጥፋትና የመፍረስ አደጋ እንደተጋረጠበት አስታውቀዋል፡፡ ''የአምባውን ታሪካዊነት የሚመጥን መሰረተ ልማት አለመሟላት ጎብኝዎች ወደ አካባቢው እንዳይመጡ እያደረገ ነው'' ያሉት ደግሞ የተንታ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አያሌው ናቸው፡፡ "በምግብ ማብሰል፣ በመንገድ መምራት፣ በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ የተሰማሩ  የማኅበሩ አባላት ተስፋ እንዲቆርጡ አድርጓል" ብለዋል ። በደቡብ ወሎ ባህልና ቱሪዝም  መምሪያ የቅርስ መዳረሻ ልማት ባለሙያ  አቶ ካሳ መሐመድ በክልሉ ገጠር መንገድ ኤጀንሲ የሚሰራው የጥገና ስራ ጥራቱን የጠበቀ ባለመሆኑ መንገዶ ቶሎ ቶሎ ለብልሽት እንደሚዳረግ ጠቁመዋል። አምባውና አካባቢው የአጼ ቴዎድሮስና የደጃዝማች ገብርዬ የቀብር ቦታ ያለበት፣ የሴባስቶፖል መድፍ የሚገኝበት፣ አውሮፓዊያን እስረኞች የታሰሩበትና በጄኔራል ናፒየር የተመራው የእንግሊዝ ጦር ውጊያ ያደረገበት ስፍራ መሆኑን ተናግረዋል ። "ስፍራው ለአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ዜጎች የቱሪስት መዳረሻ መሆን ቢችልም በሚፈለገው ደረጃ አለማም" ብለዋል ። "በአካባቢው 15 የመኝታ ክፍሎች ያሏቸው ስምንት ሎጂዎች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጎባቸው ቢገነቡም በመንገዱ አለመሰራት አስፈላጊውን አገልግሎት መስጠት አልቻሉም" ሲሉም ተናግረዋል ። የወሎ ገጠር መንገድ ጥገና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዱባለ አብራሬ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በየዓመቱ ለመደበኛ የጥገና ስራ የሚመደበው በጀት አነስተኛ በመሆኑ ለጥራት ጉድለቱ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል ። "በዚህ አመት በጀቱን በማብቃቃት ለመንገዱ ተገቢውን ጥገና ለማድረግ ታቅዷል " ያሉት ኃላፊው የጥገና ስራው በጥር 2011 አ.ም እንደሚጀመር አመላክተዋል ። "የአካባቢው መልከዓ ምድር ተዳፋት መሆን መንገዱ በጎርፍ እንዲጠቃ ምክንያት ሆኗል" ያሉት ኃላፊው የወረዳው አስተዳደር የተጠናከረ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ በማካሄድ መንገዱን ሊታደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም