የመብራት አገልግሎት በመቋረጡ ተቸግረናል - የወልድያ ከተማ ነዋሪዎች

57
ወልድያ ህዳር 20/2011 በወልድያ ከተማ ቀበሌ 05 ከሁለት ሳምንት በላይ የመብራት አገልግሎት በመቋረጡ መቸገራቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የቀበሌው ነዋሪዎች ገለፁ፡፡ በትራንስፎርመር መቃጠል ምክንያት የተቋረጠውን የመብራት አገልግሎት ስራ ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን በወልድያ መብራት ሃይል የደንበኞች አገልግሎት መስጫ ማእከል አስታውቋል፡፡ የከተማው ነዋሪ ተወካይ አቶ ገበያው ተበጀ ለኢዜአ እንደገለጡት በመብራት መቋረጥ ምክንያት በእንጨትና ብረታብረት ስራ፣ በዳቦ ቤቶች፣ ምግብ ቤት ስራ በተሰማሩ ነዋሪዎች ችግር አስከትሏል፡፡ማብሰያና ለሞባይል ባትሪ ለመሙላት አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህ የመብራት መቋረጥ ችግር ከ3ሺ በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች ችግር ላይ መውደቃቸውን አመልክተው፤ የሚመለከተው አካል አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። ሌላው የቀበሌ 05 ነዋሪዎች ተወካይ አቶ ሰሎሞን ጸጋየ በበኩላቸው በመብራት መቋረጥ ምክንያት ህብረተሰቡ ለተለያየ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር የዳረገ ከመሆኑም በላይ ወቅታዊ መረጃዎችን ማግኘት እንዳልቻሉም አመልክተዋል፡፡ ችግሩን አስመልክተው ለሚመለከተው አካል ቢያሳውቁም አስካሁን ምላሽ እንዳላገኙ የገለፁት ደግሞ አቶ ያረጋል አበጀ ናቸው፡፡ በወልድያ መብራት ሃይል የደንበኞች አገልግሎት መስጫ ማእከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ ጌታቸው ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በትራንስፎርመር መቃጠል ምክንያት የተቋረጠውን የኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡                                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም