ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በአፍሪካ የሊደርሺፕ መጽሔት የዓመቱ ምርጥ አፍሪካዊ ሽልማት እጩ ውስጥ ገብተዋል

73
አዲስ አበባ ህዳር 20/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአፍሪካ የሊደርሺፕ መጽሔት የ2018 የዓመቱ ምርጥ አፍሪካዊ ሽልማት እጩዎች ውስጥ ተካተዋል። ሽልማቱ በተለያዩ ዘርፎች የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የአፍሪካ የቢዝነስ፣ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ሰዎች እውቅና የሚሰጥ ነው። የሽልማቱ አሸናፊ የሚለየው በመጽሔቱ ድረ ገፅ ላይ በሚሰጥ ድምፅ ሲሆን ድምጽ የሚሰጡት የመጽሔቱ አንባቢዎች ናቸው። እስከ አሁን በተሰጠው ድምጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ 97 ነጥብ 31 በመቶ በማግኘት ተፎካካሪዎቻቸውን እጅግ ሰፊ በሆነ ልዩነት በመምራት ላይ ይገኛሉ። እንዲሁም የቀድሞው የቦትስዋና ፕሬዚዳንት ሴሬትሳ ካማ ኢያን ካማ 1 ነጥብ 99 በመቶ፣ የነዳጅ ላኪ አገሮች ድርጅት ዋና ጸሐፊ ናይጄሪያዊው መሐመድ ሳኑሲ ባርኪንዶ 0 ነጥብ 70 በመቶ ድምጽ አግኝተዋል። ድምጽ የሚሰጥበት ጊዜ እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሽልማቱን ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። የአፍሪካ የሊደርሺፕ መጽሔት መቀጫውን በእንግሊዝ ያደረገ እና በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ የሚሰጥ መጽሔት ነው። የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ የ2017 የመጽሔቱ የዓመቱ ምርጥ አፍሪካዊ ሽልማትን ማግኘታቸው የሚታወስ ነው። ኢትጵያዊቷ የንግድ ስራ ፈጣሪ እና የሶል ሬብልስ ጫማ አምራች ኩባንያ መስራችና ባለቤት ቤተልሄም ጥላሁን እና የታንዛንያ ታንጄት አቪዬሽን ዋና ዳይሬክተር ሱዛን ማሺቤ የመጽሔቱ የ2017 የዓመቱ ምርጥ ሴት አፍሪካዊ ሽልማትን ማግኘታቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም