በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩት አመራሮች ላይ ፖሊስ የጠየቀው የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ለነገ አደረ

65
አዲስ አበባ ህዳር 19/2011 በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) አመራሮች ላይ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ለመፍቀድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት ለነገ ቀጠረ። ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁሩንዴን ጨምሮ ከሜቴክ ጋር በተያያዘ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 26 ሰዎች ላይ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀን እንዲፈቀድለት ፖሊስ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት ከጠበቆቻቸው ጋር የቀረቡት ተጠርጣሪዎች ፖሊስ ያቀረበው ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ተገቢነት እንደሌለው ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል። ምርመራው ለአምስት ወራት ተካሂዶ መጠናቀቁን በፌዴራል ዐቃቤ ህግ መገለጹን ጠበቆቹ ለችሎቱ አስረድተዋል። ለሁሉም ተጠርጣሪ ተመሳሳይ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቅ የለበትም፤ በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ላይ በግልጽ ድርጊቱ አልቀረበም ሲሉም ተቃውመዋል። ተቋሙን ከለቀቁ የቆዩ ስላሉ የሰነድ ማስረጃ የሚያሸሹበት ምክንያት የለም፤ ማስረጃ ከመንግስት ተቋም ስለማይጠፋ ተጠርጣሪዎቹን አስሮ ማቆየት ተገቢነት የለውም በማለት የተከራከሩት ጠበቆቹ በተጠርጣሪ ቤተሰቦች ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑንም አስረድተዋል። ተጠርጣሪዎቹን በተናጠል በመጥቀስ ከጤናና መሰል ግላዊ ምክንያቶች ጋር በተያያዘ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርበዋል። ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ቢለቀቁ ሐብት ያሸሻሉ፣ የሰነድ ማስረጃ ያጠፋሉ እንዲሁም ምስክሮችን ያባብላሉ ሲልም ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ በማቅረብ ጠበቆቹ የጠየቁትን የዋስትና ጥያቄ ተቃውሟል። በመርማሪ ፖሊስና በተጠርጣሪ ጠበቆች መካከል የነበረው ክርክር መደበኛ የችሎት ሰዓት ባለመጠናቀቁ ፖሊስ በጠየቀው የጊዜ ቀጠሮ ላይ ብይን ለመስጠት ችሎቱ ለነገ ቀጠሮ ሰጥቷል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም