በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የሩሲያዊው ጠፈርተኛ ዩሪ ጋጋሪ ምስለ ቅርጽ በኢትዮጵያ ተቀመጠ

1592

አዲስ አበባ ህዳር 19/2011 ወደ ህዋ በመጓዝ ፈርቀዳጅ የሆነው ሩሲያዊ ጠፈርተኛ ዩሪ ጋጋሪን ምስለ ቅርጽ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ተቀምጧል።

በአለም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ህዋ በመጓዝ ፈርቀዳጅ የሆነው ሩሲያዊ ጠፈርተኛ ዩሪ ጋጋሪን ምስለ ቅርጽ የተቀመጠው በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት ዋና መስሪያ ቤት ነው።

ምስለ ቅርጹ በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲና በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት በጋራ በመሆን ነው የተቀመጠው።

እ.አ.አ በ1961 በሰው ልጅ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ህዋ የተጓዘው ሩሲያዊ ጠፈርተኛ ዩሪ ጋጋሪን ለህዋ ምርምር ያደረገውን አስተዋጽኦ ለአለም ለማስተዋወቅና ታሪክና ባህልን እንዲጠብቅ በማድረግ የምስለ ቅርጹ መቀመጥ ጉልህ ሚና አለው ተብሏል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያና ሩሲያ የ120 ዓመት ጠንካራ ዲፕሎማቲክ ግንኙነት ያላቸው አገሮች ናቸው።

ይህም ወደ ህዋ በመጓዝ ፈርቀዳጅ የሆነው ሩሲያዊ ጠፈርተኛ ዩሪ ጋጋሪን ምስለ ቅርጽ በኢትዮጵያ መቀመጡም ሁለቱ አገሮች ያላቸውን የረዥም አመት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያጠናክር ከመሆኑም ባሻገር በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ያላቸውን ትስስርም እንደሚያሳድግ ገልጸዋል።

“ዩሪ ጋጋሪን በአለም ላይ በስፔስ ሳይንስ ኢንዱስትሪ ላሉ ሙያተኞች፣ ሳይንቲስቶች፣ መሃንዲሶችና ለሌሎችም ታላቅ አርአያ የሚሆን ሙያተኛ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

“የስፔስ ሳይንስ ኢንዱስትሪ ለአንድ አገር ሁለንተናዊ እድገት መረጋገጥ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተር ነው” ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ ናቸው።

ዩሪ ጋጋሪን በህዋ ምርምር በአለም ታሪክ ትልቅ አሻራ ጥሎ ያለፈ ሙያተኛ ሲሆን በኢትዮጵያ ላሉ መሃንዲሶችና ሌሎች የዘርፉ ሙያተኞችም ጥሩ መነቃቃትና ጥንካሬን የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ሚስተር ቬስቮሎድ ካቼኖ በበኩላቸው ሩሲያ ከኢትዮጰያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትሰራ ገልጸዋል።

በዚህም በህዋ ሳይንስ ዘርፍ የተለያዩ የህዋ ላይ ተመራማሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ዘርፉ በአገሪቱ እንዲያድግ ለማድረግ ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።

የዩሪ ጋጋሪ ምስለ ቅርጽ “Dialogue of culture-United World” በተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት አማካኝነት በአለም ላይ ከ23 አገሮች በላይ በተለያዩ የትምህርት ተቋማት፣ ሙዚየሞችና በሌሎችም ቦታዎች በማስቀመጥ ስፔስ ሳይንስና የራሺያን ግንኙነት የማጠናከር ስራ እየሰራ ይገኛል።