ሰላምን በሰላም…

2063

በሰውነት ጀምበሩ (ኢዜአ)

በሰንበት፣ በሰንበት ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ ከታላቁ አንዋር መስጊድ አዛን፣ ከደብረ አሚን ተክለ ሀይማኖት ኪዳን ስሰማ ነፍሴ ሀሴት ታደርጋለች። የቀን ውሎየም ሰላም እንደሚሆን የመተማመን ስሜት ላይ እሆናለሁ። የሁሉም ጉዳይ ለየቅል በመሆኑ፤ ግማሹ ለሸገር ‘ጤናማነት’ ፍሬሽ አትክልት ለማቅረብ ወደ መዲናችን አትክልት ተራ ሲጓዙ፤ ከፊሉ ደግሞ እንደየእምነቱና አጥቢያው ጸሎቱን  ሊያስታኩት ወደ ጎላ ሚካኤል፣  በኒን መስጊድ ወይም ወደ ደብረ አሚን ያመራል፡፡ በአዘቦት ቀናት ተማሪዎች ቦርሳቸውን አንግተው በአቅማቸው ሲሪየስ ቦጭቀው ወደ ትምህርት ቤት፤ ሠራተኞቹ ደግሞ አንድ በመቶ   በግል መኪናቸው፤ ዘጠና ዘጠኙ እኛ እንዲሁ  በአውቶቢስ፣ በታክሲ እና በእግር ወደ ቢሯችን ስንሄድ የሰላምን ነፋስ ያለከልካይ እየማግን ነው፡፡

ሰርቶ መግባት፣ ዘርቶ መቃም፣ ወልዶ መሳም፣ የወለዱት አድጎ በማዕረግ ሲመረቅ፣ በወግ ሲዳር ማየትን የመሰለ ምን አለ?  በበዓላት ቤተዘመድ፣ ጎረቤት፣ ተሰብስቦ መጫወት፤ ጎረምሶች በአውራ ጎዳና፣ በካምቦሎጆ፣ ቆነጃጅት  በየካፍቴሪያው፣ በየሲኒማው፣ በየገበያው  ሲዝናኑ ከማየትን በቀር ምን ደስ ያሰኛል? ከሚዲያው በጎ በጎውን መስማትም ያማረ ወይን እንደቀመሰ ጎልማሳ ያደርጋል፡፡ ከሁሉም ግን አንደ ህፃናት ጨዋታና የአንገት ስር ሽታ የሚማርክ የለም፡፡ ይህም የሰላምን ወጋ ከፍ ያደርገዋል፡፡  ሰላም መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ማኀበረሰባችንም የሰላምን ዋጋ ያውቃታል፡፡

አሁን አሁን ግን እንደአለመታደል ሆኖ ሰላምን ብንፈልገውም እንኳን በተጀመረው የለውጥ እስትንፋስ ለማጣጣም የታደልን አይመስልም። በአገራችን በተለይ ላለፉት ሁለትና ሶስት አመታት በየቦታው በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት የሰላም አየር ከመጥፋቱም በላይ የሰዎች ህይዎት ሲጠፋ፣ ንብረት ሲወድም መቆየቱ የአደባባይ ሚስጢር ሆኖ ቆይቷል።  ካፉት ሰባት ወራት ጀምሮ ግን ህዝቡ እንደ አገር የሚፈልገውን ነገር ያገኘ ቢሆንም በአንዳንድ ሰላም ወዳድ ባልሆኑ ሰዎች እና ቡድኖች ምክንያት የተፈለገውን ያህል ሰላም በአገሪቱ ሊሰፍን አልቻለም።

በዚህ ከባቢ አየር የምንኖር ሰዎች ይህችን ‘ሰላማችንን’ እንዳንነጠቅ እንፈልጋለን፡፡ አደፍራሾችንም በጽኑ እንቃወማለን፡፡ ስለድህነት፣ ጠኔ፣  ሰብዓዊ መብት፣ የዜግነት መብት፣ ስለ ምስኪን ገበሬዎች፣ ስለስደተኛ ወገኖቻችን፣  ስለሴተኛ አዳሪ እህቶቻችን፣ ጎዳና ተዳዳሪ ወንድሞቻችን፣  የባህር በር፣ የዋጋ ንረት፣ የኑሮ ውድነት፣ ሀሳብን በነጻነት መግለጽ፣ የህግ የበላይነት፣ ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር፣ ሙስና፣ የትምህርት ጥራት፣ የጤና መርሐ ግብር የመሳሰሉት ነገሮችን በማንሳት እንደ ኩሬ ውሃ የረጋውን ህይወታችንን እንዲበጠብጥ አንፈቅድለትም፡፡ ጋዜጣውን አናነብም መካነ ድሩን አንከፍትም፡፡ ደፈር ብሎ “ምነው?” ብሎ  የሚሞግት ሲመጣ “አቦ!!! ሰላሜን ስጠኝ” እንላለን፡፡

መተማመን ላይ የተመሰረተ ንግግርና ውይይት ማድረጉ አስፈላጊ በመሆኑ በባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ በአዲስ አበባ የምሁራን፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ የህዝብ ተወካዮችና ዲያስፖራዎች በተገኙበት ‹‹የፖለቲካ ለውጡን እንዴት እናስቀጥል›› በሚል ርዕስ በኢኮኖሚክ ኮሚሽን አፍሪክ አዳራሽ ውይይት የተደረገው። እንደ አገር ሲታሰብ ይህ አይነት ውይይትና የሀሳብ ፍጭት መደረጉ በተሳታፊዎች መካከል የሀሳብ መቀራረብ ከመፍጠሩም በላይ ለመንግስት እንደ ግብዓት የሚሆኑ አገራዊ አንድምታ ያላቸው አጀንዳዎችን የሚያቀርብ መድረክ ነው በማለት በመድረኩ የተገኙ ምሁራን የተናገሩት።

ሰላም ምንድን ነው ?

Peace የተሰኘው ቃል ሰላምን ለመግለጽ በምሁራን ዘንድ ለመግባቢያነት የዋለ ቃል ነው፡፡ መነሻቸው በማቴዎስ ወንጌል በተራራው ስብከት  የሚገኘው በግዕዝ ‹‹ ብፁዓን ገባርያነ ሰላም”፣ ‹‹በአማርኛ ዕርቅን የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው”፣ በእንግሊዘኛው  Blessed are the peacemakers  የተሰኘው ገጸ ንባብ ነው፡፡ ማንም ጤናማ እና በጎ ህሊና ያለው ሰው ይህ ሰላሙ እንዲጠፋበት አይፈልግም፡፡ ፈላስፎች፣ የሐይማኖት መሪዎች ፣ ሳይቲስቶች  ብዙዎች ዋና ጉዳያቸው አድርገውታል፡፡

ታላላቆቹን ሳይንቲስቶች አልፍሬድ ኖቤል እና አልበርት አንስታይንን ጨምሮ ማርቲንሉተር ኪንግ፣ ሊዮ ቶልስቶይቮልቴር ሩሶ፣ መኀተመ ጋንዲ፣ ሄነሪ ዴቪድ ቴሮው፣ በርትራንድ ሩሴል፣ ኢማኑኤል ካንትጆንራውል፣ ጄን ሻርፕ፣ ዳላይ ላማ  የተሰኙት ታላላቅ ሰዎች ይሄን  ተግባር ከንደፈ ሀሳብ ጋር አጣምሮ ከያዘው ትርክት ጋር ስማቸው ተደጋግሞ ከሚነሱት ውስጥ ይመደባሉ፡፡ የአለም ታላላቅ እምነቶች የግሪክ ፈላስፎችን ጨምሮ የሰው ልጅ ሰላምን ፍጹም ለማድረግ እንዲሁም እርስ በርሱ እንዴት መኖር እንዳለበት  የተለያየ ንድፈ ሀሳብ ቀርጸዋል፡፡

ክርስቲያኖች አንቀጸ ብፁዓንን ጠቅሰው ስለሰላም ያላቸውን አቋም ሲያብራሩ ሒንዱዎች እንዲሁም ቡድሒስቶች አሒምሳ (ahimsa) ወይም ነውጥ አልባነትን(nonviolence) እንደዋና የሞራል ህግ ያስቀምጣሉ፡፡ ፕላቶም በበኩሉ  ሁላችንም አብዛኛውን የህይወታችንን ክፍል፣ ምርጥ ምርጡን ልናበረክትለት የሚገባው ለሰላም እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ናዚ መራሹ ፋሲሽዚም፣  አፓርታይድ፣  የጥቁሮች መብት በሰሜን አሜሪካና የነ አልቃይዳ አለም አቀፍ ሽብርተኝነት ከሞላ ጎደል አለም በህብረት ካወገዛቸው የቅርብ ጊዜ ነውጦች ወስጥ ይመደባሉ፡፡

የሰውን ህሊና የሚያሳርፈው ገንዘብ አይደለም፤ ንብረትም አይደለም፤ ምክንያቱም ሁሉ ነገር እያላቸው ሰላም ያጡ ሰዎች በሕይወታቸው ደስተኛ ሳይሆኑ በጭንቀት ማዕበል ተውጠው ሲቸገሩ አይተናልና፡፡ ለህሊና ዕረፍት ሰላምን ገንዘብ ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ይሆናል፡፡ ይህ ሰላም ደግሞ እንዲሁ በቀላሉ የሚመጣ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ግለሰብ በጎ ህሊና ሲኖረውና ለሰላም ሲተባበር ነው፡፡

“ረሃብን የሚያውቀው የተራበ ብቻ ነው” ይባላል፡፡ የሰላምን ምንነትና ዋጋ የሚያውቀውም ሰላም አጥቶ የነበረና ያጣ ሰው/ማኅበረሰብ ነው፡፡ እስኪ ሁላችንም በሰላም እጦት ጊዜ ምን እንደተሰማን ራሳችንን እንጠይቅ? እርግጠኛ ነኝ ኑሮውም፣ ሥራውም፣ አጠቃላይ ሕይወት ያስጠላል፡፡ ያለሰላም ደስታ የለምና!

ሰላም የሁሉ ነገር ቀዳሚ ነው፡፡ ሰላም ያለበት ማኅበረሰብ የመከባበር፣ የመተማመንና ሠርቶ የመኖር ባለቤት ይሆናል፡፡ ሰላም ከሌለ ሕይወትም ይሁን ንብረት የባለቤቱ አይሆንም፡፡ የሰላም አየር በሌለበት እንኳንስ ስለ ልማትና ብልጽግና ማሰብ ይቅርና ወጥቶ ለመግባትም ዋስትና አይኖርም፡፡ ይህንን መረዳት የሚቸግረው ሰው አለ ብሎ ማሰብ እጅግ ከባድ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ያገኘችው ሰላም እንዲህ በቀላሉ የተገኘ አለመሆኑን ጠንቅቆ ማወቅም የሰላምን ዋጋ እንዳንዘነጋው ያደርገናል፡፡ አገሪቱ ነፃነቷን ጠብቃ እንድትቆይ ከማድረግ ጀምሮ አሁን ላገኘችው ሰላም የተከፈለው የሕይወት መስዋዕትነት በዋጋ የሚተመን አይደለምና፡፡

መቼም አገሩን እንደነሶሪያ “ሰላም የራቃት ምድር” መባልን የሚሻ ያለ አይመስለኝም፡፡ በአብዛኛው የዓረቡ ምድር በሰላም እጦት ታምሶ የኮሽታ ድምፅ በተሰማ ቁጥር እየበረገገ፣ አገሩን፣ ወገኑን፣ ዘመዱን፣ ንብረቱን ጥሎ እየተሰደደ ከባህሉ፣ ከወጉ፣ ከእምነቱ፣ በአጠቃላይ ከማንነቱ ጋር ከማይመስለው ኅብረተሰብ ጋር ተቀላቅሎ ይኖራል፡፡ ይህም ዕድሜ የሰጠው ብቻ ነው፡፡ አብዛኛው ደግሞ በስደቱ የዱር አውሬ እራት ሲሆን፣ ሌላው በረሃብ ጠኔ በረሃው ላይ ወድቆ ለአሞራዎች ሲሳይ ሲውል፣ በባህር ላይ የሸሸው ደግሞ ውኃ በልቶት በዛው ሲቀር ሰምተናል፤ ተመልክተናል፡፡

የሰላም እጦት ትርፉ ይህ ነው፡፡ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሰላም አጥተው፣ ዜጎቻቸውን ለሞት ገብረውና የተረፉትንም በየቦታው ለስደት በትነው ለሰቆቃ የዳረጉት አገሮች ለዚህ ነገር ምስክሮች ናቸው፡፡ እነዚህ አገሮች ራቅ አድርገው ማሰብ ተስኗቸው አንዴ ከእጃቸው ያመለጣቸውን ሰላም ለመመለስ ቢታገሉም አልሆነላቸውም፡፡ ይባስ ብሎም “ሰላማቸው መቼውንም የሚመለስ አይመስልም” እየተባለ ሥጋት አዘል መርዶ ይነገርባቸዋል፡፡

ዛሬ እኛም “በእጅ የያዙት ወርቅ ከመዳብ ይቆጠራል” ለሚለው አባባል መተረቻ እንዳንሆን ቆመን ማሰብ አለብን፡፡ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች እያንዣበበ ያለውን ግጭት ልብ ልንል ይገባል፡፡ በእንጭጩም ለመቅጨት መንግሥት የሕዝቡን የልብ ትርታ ሊያዳምጥ ይገባል፡፡ ማህበረሰቡም እንደ ቦይ ውኃ ዝም ብሎ መፍሰስ ሳይሆን ሰላማዊ በሆነ መንገድ በእውቀት ላይ በተመሠረተና በሕግ አግባብ ጥያቄውን ማቅረብ ይኖርበታል፡፡  ለሰላም እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን አይተን እንዳላየን የማለፍ ሞራሉም ሆነ መብቱም የለንምና፡፡ ምክንያቱም በከባድ መስዋዕትነት የተገኘው ሰላም አንዴ ከእጃችን ካመለጠ ለመመለስ እጅግ በጣም ከባድ ይሆናል፡፡ በቀጣይም ኢትዮጵያንም እንደ ኢትዮጵያነቷ ለማየት ያስቸግራል፡፡

በመሆኑም በሀገራችን የተለያዩ ሳይንሳዊ እና ሀይማኖታዊ ውይይቶች ለበርካታ አመታት ጆሮ ተነፍገዋል፡፡ ለዚያም ይመስላል የተግባባን ብንመስልም ያልተግባባን፤ የተስማማን መስለን ያልተስማማን የበዛን። ዜጎች ለተሻለ ነገር የተሻለ ሀሳብ ማውጣጣት መቻላቸው የግድ ነው ‘ጋን በጠጠር ይደገፋል’ አይደል ተረቱ።

ብዙዎቻችን ግን የዝምታ ዘመቻ የሚያመጣውን ቀውስ አልተረዳንም፡፡ ሰለ ሰላም ለማሰብ ፈላስፋ መሆን አይጠይቅም፡፡ በዕለት ተዕለት ኑሯችን የሚያጋጥመን ነው፡፡ እኛ ግን አይናችንን ጨፍነናል፡፡ ሳር ቅጠሉ ግን ሰላም በሀገር እንደጠፋ ያሰረዳሉ፡፡ በቤታችን፣ በትምህርት ቤት፣ በመስሪያ ቤታችን፣ በየቤተ እምነቱ የሰላም እና የሰላም  ፍሬ ያለህ በማለት ያስተጋባሉ፡፡

የኢትዮጵያን ሰማይ ብቻ አይደለም፣ ዓለምን ፍቅርና ሰላም እርቋት እርቃኗን ከቆመች ሰነባብታለች፡፡ በአደባባይ ሰላም ተነጋግረው፣ ተሳስቀው፣ ተቃቅፈው፣ አብረው በልተው፣ አብረው ጠጥተው፤ ቤታቸው ሲገቡ ግን ሚሳዬል የሚያስወነጭፉ መሪዎች ዓለምን ሞልተዋታል፡፡ ‹‹ሰላም›› ሳይኖር-ስለ ሰላም የሚዘምሩ፣ ልባቸው ውስጥ መርዝ ታቅፈው-ማር በሚያወሩ ባተሌዎች ዓለም ተሞልታለች፡፡ የልብ ሰላም ጠፍቷል፡፡ ከልቡ ሰላም የሚል፣ ከልቡ ይቅር የሚል፣ ከልቡ የሚናገር ሰው ነጥፏል፡፡

በከንፈራችን ሁሉ ነገር ሰላም፣ ሁለ ነገር ዓለም ነው፡፡ በልባችን ውስጥ ግን ‹‹ትልቅ የጥላቻ፣ የክፋት፣ የአውሬነት ሰልፍ አለ››፡፡ ልባችን ውስጥ የሰቀልናቸውን ሰዎች፣ እንደ ይሁዳ አቅፈን በስስት እንስማቸዋለን፡፡ ‹‹ሰላም›› የለም ግን ‹ሰላም ሰላም› እንላቸዋለን፡፡ ከቤተ እምነት እስከ ቤተ መንግስት፣ ከጎዳና እስከ ሰገነት፣ ከመሃይም እስከ ምሁር፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሁለንተዊ ህይወታችን አርቲፊሻል እና የማስመሰል ባሪያ ሆኗል፡፡

የህግና የሃይማኖት ስርዓት፣ የአስመሳዮች ማታላያ፣ የክብራቸው ማማለያ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ በህግ ስም ህግ የሚጥሱ፣ በወንጌል ስም-ወንጀል የሚሰሩ ሰዎች አሸን ሆነዋል፡፡ በሳቃችን ሸንግለን፣ ብዙዎችን በልባችን ቀብረናል፡፡ ጫንቃቸውን አሻሽተን፣ እንደ ኮርማ ሰውነታቸውን አሸልተናል፡፡ ሰላም ሳይኖር…..ሰላም ሰላም እንላለን፡፡ የሰላም አየር አውርተን፣ ዞር ብለን የሞት አየር እንተነፍሳለን፡፡

‹‹ ሰላም›› የቃል ሳይሆን የመሆን ፍሬ ነው፡፡ ሰላም አፋዊ ሳይሆን ልባዊ ነው፡፡ ሰላም ምስጢራዊ ሳይሆን ገሃዳዊ ነው፡፡ ሰላም ሰዋዊ ሳይሆን ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ እውነታው ግን፤ የልባቸውን በር ቆልፈው፣ቃል ከቃል እያዳቀሉ ሰላም ሳይሆን፣ ‹ሰላም ሰላም› ይላሉ።

….ሰላም እንዲሆን የልባችን በር ይከፈት፣ ህያዊት ነፍስ እንስሳዊ ባህርይን ታሸንፍ፡፡ የአፍ ሰዎች፣ አፋቸውን ሳይሆን የልባቸውን በር ይክፈቱ፡፡ ያኔ ሰላም ሲሆን ‹‹ሰላም ሰላም›› እንላለን፡፡ አቅፈን እንስማለን፡፡ አብረን እንበላለን፡፡

ስለሆነም ሰላም በምንም ዓይነት ሁኔታ በዋጋ ሊተመን የማይችልና ለድርድር ሊቀርብ የማይገባው ጉዳይ ነውና ሁላችንም ስለሰላም እናስብ፤ ሰላምን እንሻ እንጠብቃትም!!

ሰላም ለሀገራችን!